ከኢትዮጵያ መድን ጋር የግማሽ ዓመት ቆይታን ያደረገው አጥቂ ወደ ባህር ዳር ከተማ አምርቷል።
የፊታችን ቅዳሜ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሰቲን በመግጠም የ2017 የውድድር ዘመናቸውን የሚጀምሩት ባህር ዳር ከተማዎች በዛሬው ዕለት በሀገራችን የግማሽ ዓመት ቆይታ ያደረገ አንድ አጥቂ ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።
ቡድኑን የተቀላቀለው ናይጄሪያዊው ጄሮም ፊሊፕ ነው ፤ 1 ሜትር ከ92 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው የፊት መስመር ተሰላፊው ለሀገሩ ክለቦች ጂ ሊች እና ዴሰርት ስታርስ ከተጫወተ በኋላ በመቀጠል ወደ ግብፅ በማምራት በሱዝ ፣ ሶሞሀ ዴክረንስ እና ካናህ በተባሉ ክለቦች ውስጥ በመጫወት አሳልፏል።
ተጫዋቹ ጥቂት ወራትን ያለ ክለብ ካሳለፈ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻውን በ2016 አጋማሽ የኢትዮጵያው ክለብ ኢትዮጵያ መድን ላይ አድርጎ በ8 ጨዋታዎች ለ378 ደቂቃዎች ቡድኑን በማገልገል አንድ ግብ ማስቆጠሩ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ለጣና ሞገዶቹ ለመጫወት ተስማምቷል።