በመጪው ዓርብ በሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በምን መንገድ ሊቀርቡ ይችላሉ የሚለውን ሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ዳስሳዋለች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከተከታታይ ሁለት የቻምፒየንነት ዓመት በኋላ በውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮች ታጅበው በውጣ ውረዶች የተሞላ የውድድር ዓመት ያሳለፉት ፈረሰኞቹ 48 ነጥቦችን ሰብስበው 5ኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ በክረምቱም በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ለመልቀቅ ቢገደዱም ክለቡን በተጫዋችነትም ሆነ በአሰልጣኝነት ያገለገለውን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በአሰልጣኝነት ሾመው በወጣቶች የተሞላ ቡድን ገንብተዋል። ጳጉሜ 3 ቀን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሸገር ደርቢ ጨዋታን በአሜሪካን ሀገር ለማድረግ በተጓዙበት ወቅት በርካታ ተስፈኛ ተጫዋች እና ሌሎች የቡድን አባላት በመጥፋታቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እንዲሉ ከውድድሩ አስቀድሞ ትኩረታቸውን የሰረቀ አጋጣሚ ተፈጥሮባቸዋል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ባለፉት ዓመታት በመሯቸው ክለቦች ላይ እንደተከተሉት የጨዋታ መንገድ ከሆነ ረዘም ላሉ ጊዜያት ኳስ ይዘው የሚቆዩ እና ተጋጣሚን የሚቀንሱ ተጫዋቾችን እንደመምረጣቸው ከባህር ዳር ከተማ ያስፈረሙት ፍጹም ጥላሁን በክለቡ ይደምቃል ተብሎ ይታሰባል።
የሚጠበቅ ውጤት
ከዋና ስብስባቸው ከግማሽ በላይ የሆኑ ተጫዋቾቻቸውን ያጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች እጅግ ፈታኝ ጊዜ ላይ እንደመገኘታቸው የዋንጫ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ግን ቡድናቸውን በየጊዜው እየገነቡ ለመሄድ ያክል ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ወደ ላይ የመጨረስ ዕቅድ እንደሚኖራቸው ይገመታል።
ኢትዮጵያ ቡና
ያለፈውን የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች እየተመሩ ጀምረው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እሳቸውን በማባረር በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ መመራት ከጀመሩ በኋላ በጥሩ እንቅስቃሴ ድንገተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ወደ መሆን የተሸጋገሩት ቡናማዎቹ በ51 ነጥቦች 3ኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ የኢትዮጵያ ዋንጫን በማንሳት ኢትዮጵያን በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመወከል ችለው የነበረ ቢሆንም ገና በመጀመሪያው ዙር ማጣርያ ሲገቱ እጅግ ወሳኝ ከሆኑ ተጫዋቾቻቸው መካከል 90 በመቶ የሚሆኑትን በሌሎች ክለቦች በመነጠቃቸው በወጣቶች የተገነባ ቡድን ለመገንባት ሲገደዱ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ የተወሰኑ የቡድን አባሎቻቸው አሜሪካን ሀገር መጥፋታቸው የሚፈጥረው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ስኬታማ ጊዜን ሲያሳልፍ ከነበሩ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ዕረፍት የለሹ የመስመር ተከላካይ በፍቃዱ ዓለማየሁ በዘንድሮው የውድድር ዘመንም ጎልቶ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የሚጠበቅ ውጤት
ኢትዮጵያ ቡና በኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ካደረገው እንቅስቃሴ እና የሊጉ ጨዋታዎች ወደ 36 ከፍ ከማለታቸው አንጻር ያለው የቡድን ስብስብ ይህንን ተቋቁሞ ለዋንጫ መጫወት ይጠበቅበታል ብሎ የሚገምት ብዙም አይኖርም። ሆኖም ግን አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ ካላቸው የአንድ ዓመት ውል አንጻር አቅማቸውን ዐሳይተው ራሳቸውን ሊጉ ላይ ለማቆየት በተለያዩ የጨዋታ መንገዶች ቡድኑን ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ወደታች እንዳይጨርስ ለማድረግ ይጥራሉ ተብሎ ይታሰባል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በ2009 የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መውረዱን ተከትሎ ለመፍረስ የተገደደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 የከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊ የነበረውን ኢኮስኮን የስም ግዢ በማድረግ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተመለሰ በኋላ በ2015 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ሀ” ስር በመደልደል ዓመቱን በበላይነት በማጠናቀቁ ወደ ቀደመው የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን በመመለስ ጠንካራ ቡድን በመገንባት የውድድር ዘመኑን በሰበሰቧቸው 64 ነጥቦች በሻምፒዮንነት ማጠናቀቅ የቻሉ ሲሆን ኢትዮጵያንም በመወከል በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ መርሐግብሮች ላይ በመሳተፍ በመጀመሪያው ዙር በድምር ውጤት የዩጋንዳውን ክለብ ኤ ሲ ቪላን ያሸነፉ ሲሆን በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ግን በሜዳቸው የአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ስብስብ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በታንዛኒያው ያንግ አፍሪካ 1ለ0 ሽንፈት በማስተናገድ በቀጣይም ዛንዚባር ላይ ሁለተኛ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። ባለፈው የውድድር ዓመት የነበሩ እና ቡድኑን በሚገባ ያገለገሉ ተጫዋቾችን ግልጋሎት ዘንድሮም የሚያገኘው ቡድኑ ጥቂት ዝውውሮችን በማድረግ ላቅ ባለ ግንባታ ውስጥ ሆኖ ለፕሪምየር ሊጉ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
እንደ ቡድንም ይሁን በግል አቅማቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን የሰበሰበው ቡድኑ በይበልጥ ኳስን መሠረት ያደረገ አወቃቀርን የሚከተል በመሆኑ እንዳለፈው የውድድር ዓመት ሁሉ በዚህኛው ዓመትም ተመሳሳይ አቀራረብን ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከመሐል እና ከመስመር መነሻን ያደረጉ አጨዋወቶችን በይበልጥ የሚጠቀሙት አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ዘንድሮም የጋናዊውን አማካይ ባሲሩ ዑመርን እንቅስቃሴ በደንብ ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሚጠበቀው ውጤት
ለካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቀደም በማለት የቅድመ ውድድር ዝግጅት የጀመረው ክለቡ በተጠናቀቀው ዓመትም የነበሩ እና ቡድኑ ቻምፒየን ሲሆን የነበሩ ተጫዋቾች 98 በመቶው አሁንም የስብስቡ አካል መሆናቸው በዛ ላይም በዝውውር መስኮቱ የተጨመሩ አዳዲስ ፊቶችን በመያዝ ልክ እንደ 2016 የውድድር ዘመን ሁሉ ለቻምፒየንነት ዳግም በያዝነው ዓመት እንደሚፎካከር ይገመታል።
መቻል
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም ከተመለሰ በኋላ የተረጋጋ የአሰልጣኝ ቆይታን ማድረግ ያልቻሉት ጦረኞች ያለፈውን የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ከሾሙ በኋላ ዓመቱን በድል ግስጋሴ ውስጥ ሆነው በቻምፒየንኑ ንግድ ባንክ በአንድ ነጥብ ተበልጠው በ63 ነጥቦች ሊጉን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው መቋጨት ችለዋል። በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ውላቸውን ያጠናቀቁ ተጫዋቾችን ኮንትራት ያደሱት እና ቡድኑን በቋሚነት ያገለገሉ አብዛኛዎቹን ተጫዋቾች አላማጣታቸውም እንዲሁም ደግሞ ክፍተት በተስተዋሉባቸው ቦታዎች ላይ ከፈጸሟቸው ዝውውሮች አኳያ ልክ እንደ ዓምናው ሁሉ በዚህኛውም ዓመት ከተረጋጋ የቡድን መስተጋብር ጋር ሊጉ ላይ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
መቻሎች በቡድናቸው ውስጥ በርካታ ክዋክብቶችን ያቀፉ ቢሆንም ገዘፍ ባለ የግል አቅም ቡድኑን ይዘው የሚወጡ ተጫዋቾችም ባለቤት ነው። ኳስን መሠረት ባደረጉ ቅብብሎች መጫወትን የሚመርጠው ቡድኑ በማቀበሉም ሆነ ግቦችን በማስቆጠሩ ረገድ ከፍ ያለ አበርክቶን ዓምና ያደረገው ሽመልስ በቀለ ዳግም በፕሪምየር ሊጉ ላይ ይደምቃል ተብሎ ይታሰባል።
የሚጠበቀው ውጤት
ያለፈውን የውድድር ዘመን ቡድኑን ማገልገል የቻሉ ተጫዋቾች አሁንም ከቡድኑ ጋር አብረው የሚገኙለት መቻል በነበሩ ጥቂት ቀዳዶች ካደረገው የዝውውር ጥገና ውጪ ለሻምፒዮንነት ያፎካከሩለት ባለ ልምዶቹን ተጫዋቾች አሁንም መያዙ በሊጉ የዋንጫ ግስጋሴ ውስጥ ሆኖ ሊገኝ እንደሚችል መገመት ያሻል።
መቐለ 70 እንደርታ
በአስከፊው ጦርነት ምክንያት ለዓመታት ከሀገራዊ ውድድሮች ርቀው የቆዩት መቐለ 70 እንደርታዎች በ2017 የውድድር ዓመት ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሰዋል። ቀደም ብሎ ባለፈው የውድድር ዓመት ከመቻል ጋር ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬን በመቅጠር በዝውውሩ ራሱን ያጠናከረው ቡድኑ በአመዛኙ በአዳዲስ ተጫዋቾች የተዋቀረ ቡድን ይዞ ወደ ውድድሩ ይቀርባል።
ከዚህ ቀደም ከሊጉ ፈርጣማ የፋይናንስ አቅም ከነበራቸው ጠንካራ ቡድኖች ተርታ የነበረው ቡድን በቀጣይ የውድድር ዓመት እንደከዚህ ቀደም በሊጉ አናት ከሚቀመጡ ክለቦች ይሆናል ተብሎ ባይጠበቅም ከቀላቀሏቸው አዳዲስ ፈራሚዎች እና ባለፉት ዓመታት በክለቡ ስኬት ድርሻ የነበራቸው ተጫዋቾች መኖር አንጻር ከቡድኑ የተሻለ ነገር እንዲጠበቅ ያደርጋል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
እንደ አዲስ በተዋቀረ እና ከዓመታት በኋላ ወደ ውድድር ከሚመለስ ስብስብ ውስጥ ከወዲሁ ጎልቶ የሚወጣ ተጫዋች ለማውጣት አዳጋች ቢሆንም በተጫዋቾቹ የቅርብ ጊዜ አቋም መሰረት ከባህርዳር ከተማ ቡድኑን የተቀላቀለው አማካዩ የአብሥራ ተስፋዬ በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ አጨዋወት ላይ ወሳኝ ሚና ይሰጠዋል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው የውድድር ዓመት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳዩት እንደነ ቦና ዓሊ እና ቤተኞቹ ያሬድ ከበደ እና ሙሉጌታ ወልደ ጊዮርጊስም ሌሎች የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
የሚጠበቅ ውጤት
በ2010 በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ መሳተፍ የጀመሩት ምዓም አናብስት በሊጉ በቆዩባቸው ሦስት የውድድር ዓመታት ከጠንካራ ቡድኖች ውስጥ ነበሩ። ቡድኑ በከዚህ ቀደም ተሳትፎው በ2010 አራተኛ፣ በ2011 የሊጉ ቻምፒዮን እንዲሁም በ2012 የውድድር ዓመት ሊጉ በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት እስከተቋረጠበት ወቅት ድረስ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ አመርቂ የሚባሉ ቀደምት ውጤቶች ቢያስመዘግብም በዘንድሮው የውድድር ዓመት ዋነኛ ዓላማው በሊጉ መቆየት እንደሚሆን ይገመታል።
ፋሲል ከነማ
2011 ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ሦስተኛ በመሆን በዛኑ ዓመት ደግሞ የጥሎ ማለፍ አሸናፊ እንዲሆን ያደረጉትን አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ዳግም የሾሙት ፋሲል ከነማዎች በ2016 የውድድር ዘመን ከሰበሰቧቸው በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች አንፃር ብዙኃኑ የእግር ኳሱ ማህበረሰብ ቡድኑን ለዋንጫ ቢያጩትም በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ ላይ በ44 ነጥቦች ተቀምጦ ለማጠናቀቅ ተገዷል። ቡድኑ ውስጥ የነበሩ ጥቂት ተጫዋቾችን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ በመስጠት በዝውውሩ አዳዲስ ፊቶች ላይ ትኩረትን ያደረገው ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ከነበረው ጠንካራ አቀራረብ አንፃር አንዳች ነገርን በሊጉ ላይ ሊያስመለክተን ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሚጠበቀው ተጫዋች
ዐፄዎች ባለፈው የውድድር ዘመን ሁለት መልክ የነበረውን የውድድር ዘመን ከማሳለፋቸው አኳያ ከነበረው ስብስብ ውስጥ በልዩነት ነጥሮ የሚወጣን ተጫዋች መገመት ቢያዳግትም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ መልካም የሚባል እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የነበረው እና ሦስት ጎል እና ሁለት አሲስቶች ያሉት አዲሱ ዩጋንዳዊ አጥቂ ማርቲን ኪዛ ፕሪምየር ሊጉ ላይም እንድንጠብቀው ያደርገናል።
የሚጠበቀው ውጤት
በተከታታይ የውድድር ዘመናት በፉክክር ውስጥ ከሚጨርሱ ቡድኖች መካከል የሆነው ቡድኑ ዓምና የውጤት ወጣ ገባ የሚታይበት ቢሆንም በዚህኛው የውድድር ዘመን ግን ከዓምናው ክፍተቶቹ በማገገም በፕሪምየር ሊጉ የላይኛው ደረጃዎች ውስጥ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ባህር ዳር ከተማ
ባለፈው የውድድር ዓመት 50 ነጥቦችን በመያዝ 4ኛ ደረጃ ላይ ሆነው የጨረሱት ባህር ዳር ከተማዎች በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾችን ከለቀቁ ክለቦች መካከል አንዱ ሆነዋል። በተለይም ያልተጠበቁ ክስተቶች በፈጠሩት ድባቴ ውጤታማ መሆን ያልቻለው ቡድኑ በዚህ የውድድር ዓመት በጥሩ መንፈስ ተገንብቶ በቁጥር በዛ ያሉ ታዳጊዎችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል ከከፍተኛ ሊግም ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ሰንብቷል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
ወደ ክለቡ በተቀላቀለበት የውድድር ዘመን በ27 ጨዋታዎች በወጥነት ቡድኑን ያገለገለው ፍሬዘር ካሳ ከቀናት በፊት በተደረጉ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች በተለይም ከታንዛኒያ ጋር በተደረገው ጨዋታ እጅግ አስደናቂ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችል ነገ ዓርብ ለሚጀምረው ፕሪሚየር ሊግም ጥሩ መነሳሳት እንደሚፈጥርለት ይጠበቃል።
የሚጠበቅ ውጤት
ባህር ዳር ከተማ በተከታታይ ሁለት ዓመታት ይዞት ከነበረው ስብስብ አንጻር ለዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም በዘንድሮው ስብስቡ ግን በተለይም ጎል አምራች እና የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው መነሻ የነበሩት ተጫዋቾች ቡድኑን በመልቀቃቸው ዋንጫ ማንሳትን አልመው ይወዳደራሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ግን አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በተከታታይ ሁለት ዓመት የገነቡትን የጨዋታ መንገድ አስቀጥለው ቡድኑ ከወገብ በላይ እንዲጨርስ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ወልዋሎ ዓ/ዩ
እንደ ሌሎች የትግራይ ክለቦች በጦርነቱ ምክንያት ለዓመታት ከውድድር ከራቁ በኋላ ወደ ሀገራዊው ውድድር የተመለሱት ወልዋሎዎች ቀደም ብለው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመቅጠር በርከት ያሉ ዝውውሮች በመፈፀም የሊጉን መጀመር በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በቢሾፍቱ ከተማ ያከናወኑት እና በርከት ያሉ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ያካሄዱት ቢጫዎቹ በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳታፊ ከነበሩ ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ።
ባለፈው የውድድር ዓመት በክልላዊ ሊግ የተሳተፈው የወጣቶች ስብስብ እና ልምድ ባላቸው አዳዲስ ፈራሚዎች የተዋቀረ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የዚህ የውድድር ዘመን ዋነኛ ዓላማቸው ከወዲሁ በርከት ያሉ ክለቦች ይፎካከሩበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ላለመውረድ የሚደረግ ፍልሚያ ርቀው የተለመደው የክለቡ የመሃል ሰፋሪነት ቦታ ማስጠበቅ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
እንደ አዲስ በተዋቀረው የቢጫዎቹ ስብስብ ውስጥ በአሰልጣኙ ቁልፍ ሚና ይሰጠዋል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ነው። ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች በአሰልጣኝ አሸናፊ ሥር ከሠራው ፈጣኑ አጥቂ በተጨማሪም ከዓመታት በኋላ ወደ እናት ክለቡ የተመለሰው ግብ ጠባቂው በረከት አማረ እና እያሱ ለገሰ ሌሎች የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
የሚጠበቅ ውጤት
በሊጉ በቆዩባቸው ዓመታት ከመሃል ሰፋሪ ቡድኖች ውስጥ የነበሩት ወልዋሎዎች በቅርቡ በሚጀመረው አዲሱ የውድድር ዓመት ዋነኛ ዓላማቸው በሊጉ መቆየት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ከአንድ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት ኤሌክትሪኮች ባለፉት ዓመታት ለውጣ ውረድ የዳረጓቸውን ስህተቶች ለማስተካከል እና በዚህ የውድድር ዓመት ቢያንስ በሰንጠረዡ መሃል ሰፋሪነት መቆየታቸውን ለማረጋገጥ በፕሪሚየር ሊግ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች በማስፈረም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ እና በበቂ ሁኔታ የተደራጀ ቡድን ገንብተዋል። ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ከፈረሰኞቹ ጋር የሊጉን ክብር ያሳካው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን የሾመው ቡድኑ በዝውውሮቹ እና በአሰልጣኝ ቅጥሩ ጥራት ምክንያት በውድድር ዓመቱ የተሻለ ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ አቅም ገንብቷል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
ከዓመታት የፋሲል ቆይታ በኋላ ዐፄዎቹን ለቆ ኤሌክትሪክን በመቀላቀል የቡድኑ አምበል ሆኖ ማገልገል የጀመረው ሁለገቡ ሽመክት ጉግሳ በቡድኑ ጎልተው ይወጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ ነው።
የሚጠበቅ ውጤት
ኤሌክትሪኮች ምንም እንኳን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ በተመለሱበት የመጀመርያ ዓመት ላይ ቢገኙም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የቅርብ ዓመታት የዋንጫ ታሪክ ያለው አሰልጣኝ መቅጠራቸው እንዲሁም በተሻለ ደረጃ ሊያፎካክር የሚችል ቡድን መገንባታቸውን ስናይ ታሪካዊው ኤሌክትሪክ ቢያንስ እስከ አስረኛ ደረጃ ያለውን ቦታ ይዞ ይጨርሳል ተብሎ ይገመታል።