አዳማ ከተማ የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር ለመቋጨት ሲቃረብ ለማስፈረም ከተስማማቸው ሦስት ተጫዋቾች ጋር ደግሞ አይቀጥልም።
ክለቡን በቡድን መሪነት እና በረዳት አሰልጣኝነት ያገለገሉትን አቡዲ ቡሊን በዋና አሰልጣኝ ቀጥረው የቀድሞ ተጫዋች ብርሃኑ ቃሲም እና ሳሙኤል አበራን ረዳት አሰልጣኝ ካደረጉ በኋላ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በባቱ ከተማ ሲሰሩ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ክለቡ በነበረበት ዕግድ እና በክለብ ላይሰንሲንግ መመሪያ አለማሟላትን ተከትሎ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማፀደቅ ሳይችል የነበረ ሲሆን በትናንትናው እና በዛሬው ዕለት የሚጠበቅበትን በማገባደዱ አዳዲስ ተጫዋቾችን በይፋ ለማስፈረም እየተቃረበ ይገኛል። ቡድኑ ከሳምንታት በፊት ግብ ጠባቂዎቹን ዳግም ተፈራ እና ዳንኤል ተሾመን ፣ ተከላካዩን ኃይለሚካኤል አደፍርስን ፣ አማካዮቹን ዳንኤል ደምሱ እና ሙሴ ካቤላን እንዲሁም አጥቂዎቹን ስንታየው መንግሥቱ እና አሜ መሐመድን የስብስቡ አካል ያደረገ ሲሆን አሁን ደግሞ ሦስት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ቡድኑ በማካተት የአዳዲስ ተጫዋቾችን ቁጥር አስር አድርሷል።
ብሩክ ሙሉጌታ አዳማን ለመቀላቀል ተስማምቷል። በኮልፌ ቀራኒዮ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ ሲዳማ ቡና በማምራት ወደ ሊጉ ብቅ ያለው የመስመር እና የፊት አጥቂው ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ቆይታን አድርጎ ቀጣይ መዳረሻውን አዳማ አድርጓል።
ሌላኛው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ቻላቸው መንበሩ ነው። የቀድሞው የደሴ ከተማ ፣ ገላን ከተማ እንዲሁም የኢትዮጵያ መድን ተጫዋች የተጠናቀቀውን ዓመት በሻሸመኔ ከተማ አሳልፎ ወደ አዳማ ተጉዟል።
ቡድኑ ሦስተኛው ፈራሚ አድርጎ ለመቀላቀል የተቃረበው ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ ቤንች ማጂ ቡና የነበረውን ግብ ጠባቂ ናትናኤል ተፈራን ነው።
በተያያዘ ክለቡ ከዚህ ቀደም ለማስፈረም ተስማምቷቸው ከነበሩት የቀኝ ተከላካዩ ፉዓድ ሙዘሚል ፣ ከሁለገቡ አቡበከር ወንድሙ እና ከአጥቂው ስዩም ደስታ ጋር እንደማይቀጥል ዝግጅት ክፍላችን አውቃለች።