ቀሪዎቹን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የውድድር ዓመት አቀራረብ በተመለከተ የሶከር ኢትዮጵያን ዳሰሳ እነሆ!
ሲዳማ ቡና
ባለፈው የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እየተመሩ ጀምረው አሰልጣኙ ጋር በመለያየት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን የቀጠሩት ሲዳማ ቡናዎች በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ቢገቡም የኋላ ኋላ ግን 40 ነጥቦችን የማሳካት ዕቅድ ይዘው ያንንም በማሳካት በ40 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ሆነው ጨርሰዋል። ሆኖም እጅግ ወሳኝ የሚባሉ በርካታ ተጫዋቾችን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያስፈረሙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ካለፈው ዓመት በተሻለ መረጋጋት ላይ ሆነው የፊታችን ሰኞ በሮዶዋ ደርቢ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርጉትን የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
ለመከላከል ቅድሚያ በሚሰጡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሥር ጎልቶ ለመውጣት ቅርብ የሚመስለው ተጫዋች በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከባህር ዳር ከተማ የፈረመው እና የክለቡ አምበል እንዲሆን የተደረገው ያሬድ ባየህ ነው ተብሎ ይታሰባል።
የሚጠበቅ ውጤት
በተከታታይ ዓመታት በርካታ የተጫዋች ዝውውሮችን ቢያደርጉም ውጤታማነት የራቃቸው ሲዳማዎች ባሳለፍነው የውድድር ዘመን መገባደጃ ላይ ካሳዩት ጠንካራ እንቅስቃሴ እና ካስፈረሟቸው ተጫዋቾች አንጻር ለዋንጫ ከመፎካከር ውጪ የተለመደው የውጤት መዋዠቅ በደጋፊዎቹ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም።
ሀዋሳ ከተማ
ባለፈው የውድድር ዓመት በ41 ነጥቦች 9ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ኃይቆቹ እንደ ከተማ ተቀናቃናቸው ሲዳማ ቡና ሁሉ በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ አሳልፈዋል። በተለይም ቡድኑ በማጥቃት እንቅስቃሴው ጎሎችን ለማስቆጠር ባይሰንፍም በኋላ መስመሩ ላይ የነበረው ትኩረት ማጣት ግን እጅግ አሳሳቢ ነበር። በሮዱዋ ደርቢ ሰኞ ምሽት ሲዳማ ቡናን በመግጠም ፕሪሚየር ሊጉን የሚጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንጻር በመጀመሪያ ጨዋታ የሚያስመዘግቡት ውጤት ለቀጣይ ጨዋታዎች የሚፈጥረው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጎን ቀላል የሚባል አይደለም።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20 ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ክብርን የተቀዳጀው ኤርትራዊ አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ወደ ስዊድን ለማቅናት ከጫፍ ደርሶ ባለመሳካቱ ክለቡን በድጋሚ መቀላቀሉ የሚታወስ ሲሆን የባለፈውን ዓመት እንቅስቃሴው ከደገመው የክለቡ ብቻ ሳይሆን የሊጉ ድምቀት ሊሆን ይችላል።
የሚጠበቅ ውጤት
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ4ኛ ወደ 7ኛ እና ወደ 9ኛ ደረጃ እየተንሸራተተ የዘለቀው ቡድኑ ባለፈው ዓመት የተጠቀመባቸው በርካታ ተጫዋቾችን በመያዙ እና እንደ ቢኒያም በላይ እና ዮሴፍ ታረቀኝ ያሉ ቁልፍ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ከመቀላቀሉ አንጻር ያለበትን ክፍተት ሞልቶ እና ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን ገንብቶ መቅረብ ይጠበቅበታል።
አርባምንጭ ከተማ
በአሰልጣኝ በረከት ደሙ እየተመሩ ከአንድ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሱት አዞዎቹ ለወሳኙ ፈተኛ ራሳቸውን እያዘጋጁ ይገኛሉ። ዋና አሰልጣኛቸውን እና አማካዩ እንዳልካቸው መስፍንን በአሰልጣኝ እና በተጫዋች ዘርፍ የከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ያሸለሙት አርባምንጭ ከተማዎች ከነበራቸው ስብስብ በርካቶችን በማስቀጠል እና ያልተጠበቁ አዳዲስ ዝውውሮችን በመፈጸም በነገው ዕለት የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸውን ለማድረግ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ ተጫዋች
አዞዎቹ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ሲያድጉ 18 ጎሎችን በማስቆጠር ጥምር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሆነው አህመድ ሁሴን ሚና ከፍተኛ ቢሆንም የመሃል ሜዳው ሞተር እንዳልካቸው መስፍን ወደር የለሽ የሆነ የውድድር ዓመት አሳልፎ የውድድሩ ኮከብም ሆኖ ከመምጣቱ እና የክለቡን ባሕል ጠንቅቆ ከማወቁ አንጻር የተሳካ የውድድር ጊዜ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
የሚጠበቅ ውጤት
አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ሊጉ ከአንድ ዓመት በኋላ ቢመለሱም ካደረጓቸው ጠንካራ ዝውውሮች አንጻር በሊጉ ከመቆየት ባሻገር ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ከፍ ብለው የመጨረሻ ዕቅድ እንደሚኖራቸው ግን ሳይታለም የተፈታ ነው።
ሀዲያ ሆሳዕና
በክለቡ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ካስመዘገበው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ጋር በመለያየት የተጠናቀቀውን ዓመት ከዮሐንስ ሳህሌ ጋር መጀመር የቻሉት ነብሮቹ ብዙም ሳይቆዩ ከአሰልጣኙ ጋር በመለያየት በቦታው ረዳት አሰልጣኙ ግርማ ታደሠን በመተካት በ41 ነጥቦች በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ስምንተኛ ላይ ተቀምጠው ዓመቱን ማጠናቀቅ ችለዋል። በክረምቱ በጥቂት ወሳኝ ቦታዎች ላይ በዝውውሩ የተካፈለው ቡድኑ ነባሮችን ጭምር ይዞ ከቅድመ ውድድር ዝግጅቶች ባለፈ ካደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች መልስ ለፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ወደ ምስራቁ ከተማ አምርቷል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
አዘውትረው ከሚጠቀሙት የሽግግር አጨዋወት አኳያ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች ላይ ትኩረት ያደረጉት አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ በያዝነው የውድድር ዘመን እንዳለፈው ዓመት ሁሉ የወጣቱን ተመስገን ብርሃኑን ግልጋሎት መጠቀማቸው የማይቀር ከመሆኑ አኳያ ከግብፅ ሙከራ የተመለሰው ፈጣን ተጫዋች ከብሩክ ማርቆስ ጋር በአንፃራዊነት ላቅ ያለ ትኩረት ሊስብ እንደሚችል ይጠበቃል።
የሚጠበቅ ውጤት
ከአጥቂው ዳዋ ሆቴሳ በስተቀር ከለቀቋቸው ተጫዋቾች ተነስተን መገመት እንደምንችለው ቡድኑ ፈጠን ያሉ የኳስ ሂደቶች የሚከተል ቢሆንም በመከላከሉ ረገድ የሚታይበትን ጠንካራ ይዘት በማጥቃቱ ደግሞ የተገደበ ሆኖ በተደጋጋሚ መታየቱ ቡድኑ ዘንድሮም በሊጉ ወገብ ላይ ሆኖ የሚጨርስ እንደሚሆን መገመት ቢቻልም አሰልጣኙ ከዓመቱ መጀመሪያ አንስቶ ቡድኑን መረከባቸው በውድድር ዓመቱ የተለየ አቀራረብን ሊያስመለክቱን እንደሚችሉ ግን ይታመናል።
ወላይታ ድቻ
በየዓመቱ በወጣቶች የሚገነባው ወላይታ ድቻ ከ2016 የውድድር ዘመን አጋማሽ በኋላ በስብስብ ጥበት የተነሳ በሊጉ ላይ ተፎካካሪነቱ ወርዶ የቀረበበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል። የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹው ክለብ ከተጎዱበት በርካታ ተጫዋቾች ጋር እየታገለ በደረጃ ሰንጠረዡ አስራ ሦስተኛ ላይ በ34 ነጥቦች ተቀምጦ በሰሰቀን ዓመቱን ማጠናቀቁ የሚታወስ ቢሆንም በያዝነው ዓመት ላይ ግን ባደረጋቸው ዝውውሮች ያስፈልጉኛል ያላቸውን ተጫዋቾች በማስፈረም እና ከነባሮቹ ጋር በማቀናጀት ዝግጅታቸውን አገባድደዋል። አሰልጣኙ በቡድኑ ውስጥ ዓምና አብረው መኖራቸው ዘንድሮ በተጠናከረ መዋቅር አቀራረባቸውን በተለየ መልኩ ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት ግን ከባድ የሚሆን አይመስልም።
የሚጠበቀው ተጫዋች
ዘለግ ላሉ ዓመታት ረጃጅም ኳሶችን መጠቀም ባህላቸው አድርገው የነበሩት የጦና ንቦቹ ከአሰልጣኝ ያሬድ ጋር መሥራት ከጀመሩ ወዲህ መሐል ላይ መነሻቸውን ያደረጉ ኳሶች ላይ ትኩረት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን የአብነት እና ብዙዓየሁ መስተጋብር ስልቱ ከፍ ያለ ከመሆኑ አንፃር በተለይ ደግሞ በማጥቃቱ ላይ የብዙዓየሁ ሰይፈን አጨዋወት መነሻ በማድረግ አማካዩ በዓመቱ ተጠባቂ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።
የሚጠበቀው ውጤት
ቡድኑ ከ2006 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወዲህ ባሉ የሊግ ጨዋታዎች ላይ የወጥነት ችግር የሚታይበት ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚኖሩት ክስተታዊ የነጥብ መሰብሰቦች ግን አግራሞትን ሲያጭሩ ስናስተውል ቆይተናል። በ2016 የውድድር ዘመን የታችኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ሆኖ ሲዳክር የተስተዋለው ቡድኑ አብዛኛው ስብስቡ በወጣቶች የተገነባ ሲሆን ክፍተቶች አሉብኝ ብሎ ባሰባቸው ቦታዎች ላይ ያመጣቸውን ተጫዋቾች ስንመለከት ምንአልባትም የሊጉ መሐል ሰፋሪ ቦታ ላይ ተቀምጦ ሊያጠናቅቅ እንደሚችል መናገር ይቻላል።
አዳማ ከተማ
ላለፉት ሁለት ዓመታት ከግማሽ ያህል በአሰልጣኝነት ቡድኑን ከመራው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ጋር ብቻም ሳይሆን በርካታ ተጫዋቾቹን በክረምቱ ለማጣት የተገደደው አዳማ ከተማ በ44 ነጥቦች ካጠናቀቀው እና በደረጃው ሰባተኛ ላይ ተቀምጦ ከፈፀመው የ2016 ዓመት አንፃር ዓመቱ ፈታኝ እንደሚሆንበት ይጠበቃል። ካጣቸው ተጫዋቾች አንፃር ወደ ቡድኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም ከገንዘብ አከፋፋል አንፃር አሁንም ዕክሎች ያላጡት ቡድኑ ከአዲሱ አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ጋር በሚኖረው ቆይታ በእጅጉ ከዓምናው ያልተሻሻለ ቆይታ ሊኖረው እንደሚችል ከነበሩት የክረምት የቅድመ ውድድር ዝግጅቶች መረዳት እንችላለን።
የሚጠበቀው ተጫዋች
በወጣቶች በይበልጥ የተገነባው አዳማ ከተማ ዘንድሮ የአሰልጣኝ ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ የአጨዋወት ለውጥም ሊኖረው ይችላል ፣ ሆኖም በቡድኑ ውስጥ ከዓመት ዓመት ራሱን እያሳደገ የመጣው ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም ዐይተን በግልም ሆነ እንደ ቡድን ከሚያሳያቸው መልካም እንቅስቃሴዎች መነሻነት ዘንድሮም ልንጠብቀው እንገደዳለን።
የሚጠበቀው ውጤት
ቡድኑ ከነበሩት ወሳኝ ተጫዋቾች ጋር መለያየቱ የሚጎዳው መሆኑ የማይካድ ሀቅ ቢሆንም ወጣት እና የመጫወት ፍላጎት ያላቸውን ተጫዋቾች በስብስቡ መያዙ አሰልጣኙ በቡድኑ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት አብረው የነበሩ ቢሆንም የአጨዋወት መንገዳቸውን እስኪያዳብሩ ድረስ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል ተብሎ ይታሰባል። በዚህም ምክንያት በሊጉ መቆየት የመጀመሪያው ዕቅዳቸው ይሆናል ወደሚል ድምዳሜ ይወስደናል።
ወልቂጤ ከተማ
ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ጋር ያለፈውን ዓመት የነበሩ ከ95 በመቶ በላይ ተጫዋቾችን በአሁኑ ስብስብ ውስጥ ያላካተቱት ሠራተኞቹ በዚህኛውም ዓመት ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የታየባቸው ደካማ የሊግ ቆይታን መድገማቸው የማይቀር ይመስላል። የመሐል ዳኝነት ሥራውን በመተው ወደ ቀደመ የአሰልጣኝነት ሕይወቱ የተመለሰበትን ሹመት በፈፀመው ሶሬሳ ካሚል የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በሀዋሳ በነበራቸው የክረምት ዝግጅት ወቅት በርከት ካሉ ፈተናዎች ጋር ሆነው ከሃያ በላይ አዳዲስ ተጫዋቾችን የያዙ ሲሆን እንደ ቡድን ከገነቡት አዲስ የቡድን ግንባታ አንፃር ፈታኝ ዓመት ሊሆንባቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል።
የሚጠበቀው ተጫዋች
ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ቡድኑ ላይ በአዳዲስ ፊቶች ዕድሳትን ያደረገው ቡድኑ በ2016 ባሳለፈው ፈታኝ ዓመት ውስጥ እንደ መልካም የሚነሳው ወጣቱ አማካይ መድን ተክሉ በያዝነውም ዓመት ይህንን ድንቅ ክህሎት እንደሚደግም ተስፋ ሊደረግበት ይችላል።
የሚጠበቀው ውጤት
ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ እንደመቅጠሩ ብቻ ሳይሆን እልፍ ሲልም በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን መያዙ አሁንም ቡድኑ በሚኖረው የሰላሳ ስድስት ሳምንታት ሩጫ ላይ በተከታታይ ዓመታት ከታዩበት ዕክሎች ላይነፃ እንደሚችል እና በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ፉክክር ላይ በይበልጥ አሁንም ልንመለከተው እንደምንችል መገመት ከባድ አይሆንም።
ስሑል ሽረ
ከዓመታት በኋላ ወደ ሀገራዊ ውድድር መመለሳቸውን ተከትሎ ቀደም ብለው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ቀጥረው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት ስሑል ሽረዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት ንቁ ተሳትፎ ካደረጉ ክለቦች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ሽረዎሽ በቂ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሳያደርጉ ወደ ውድድሩ መግባታቸው እንደ አንድ ደካማ ጎን የሚጠቀስላቸው ቢሆንም
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
የስሑል ሽረ ሁለተኛ ቡድን ውጤት የሆነውና ዳግም አሳዳጊ ቡድኑን ለማገልገል የተመለሰው የመሀል ተከላካዩ ነፃነት ገብረመድኅን እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ ስሑል ሽረን የተቀላቀለው ኤልያስ አሕመድ ከቡድኑ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
የሚጠበቅ ውጤት
የስሑል ሽረ የውድድር ዓመቱ ዋነኛ ዓላማ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ለቀጣይ ውድድር ዓመት ማስቀጠል እና በሊጉ መቆየት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በመጀመርያው ዓመት የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ተቸግረው በሁለተኛው ዓመት ጥሩ ቡድን የገነቡት ሽረዎች በታሪካቸው ለሦስተኛ ጊዜ በሊጉ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ መድን
ባለፈው የውድድር ዓመት ሁለት መልክ ያለው የውድድር ጊዜ ያሳለፉት መድኖች በመጀመርያው ዙር በተከታታይ ነጥብ ቢጥሉም በሁለተኛው ዙር በርከት ያሉ ዝውውሮች ፈፅመው ደረጃቸው በማሻሻል በዙሩ ብዙ ነጥብ ከሰበሰቡ ክለቦች ተርታ ተመድበዋል። መድን ምንም እንኳ በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ ባያደርግም ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ስብስቡን በሚገባ ማጠናከሩን ከግምት ውስጥ ስናስገባ ቡድኑ በጥንካሬውን የሚቀጥልበት ዕድል የሰፋ ነው።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
በአሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ አጨዋወት ቁልፍ ሚና ከሚሰጣቸው ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አማካዩ ወገኔ ገዛኸኝ ዘንድሮም የሚጠበ2 ተጫዋች ነው።
የሚጠበቅ ውጤት
መድኖች ባለፈው የውድድር ዘመን ሁለተኛው ዙር ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ ማስቀጠል የሚችሉ ከሆነ ዘንድሮ ከብዙዎች ግምት ውጭ በሰንጠረዡ አናት ላይ ሆነው የሚጨርሱበት ዕድል አለ።
ድሬዳዋ ከተማ
ባለፈው የውድድር ዓመት ከአዳማ ከተማ ጋር ውጤታማ ጊዜ ያሳለፈው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በመቅጠር ወሳኝ ዝውውሮች ያገባደዱት ብርቱካናማዎቹ ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ ጥንካሬ ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል። ቡድኑ እንደ አዲስ መዋቀሩ ከሚገጥመው ውስን የውህደት ችግር ውጭ ለዋንጫ መፎካከር የምያስች በጥራትም በጥልቀትም የተሻለ ስብስብ ገንብቷል።
ጎልቶ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋች
በክረምቱ የዝውውት መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ ብርቱካናማዎቹን የተቀላቀለው መሐመድ ኑር ናስር በቡድኑ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው። በባለፈው የኢትዮጵያ ቡና ስኬት ትልቅ ድርሻ የነበረው ተጫዋቹ የቡድኑ የፊት መስመር ይመራል ተብሎም ይጠበቃል።
የሚጠበቅ ውጤት
ብርቱካናማዎቹ እንዳለፉት ዓመታት ላለመውረድ ከመፎካከል በዘለለ ከወገብ በላይ ባለው ፍክክር ራሳቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይገመታል።