ዛንዚባር ላይ የሚደረገውን የያንጋ እና ባንክ ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

በነገው ዕለት ያንግ አፍሪካንስ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ የስታዲየም መግቢያ ትኬት ተሸጦ ሲያልቅ የጨዋታው ዳኞችም ታውቀዋል

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆን ሀገራችንን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እየወከለ የሚገኘው ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ የዩጋንዳውን ቪላ በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ በሁለተኛው ዙር የታንዛኒያውን ኃያል ክለብ ያንግ አፍሪካንስ ያገኘ ሲሆን ከቀናት በፊት አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታም ቡድኑ አንድ ለምንም ተሸንፏል።

በነገው ዕለት በዛንዚባሩዋ አማኒ ኮምፕሌክስ ስታዲየም የሚደረገውን የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ በአካል ለመከታተል የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች ቀድመው ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን ትኬቶቹም ዛሬ ረፋድ ተሸጠው ማለቃቸው ተገልጿል።

ይህንን ጨዋታ አራት ሞሪታኒያዊ አልቢትሮች የሚመሪት ሲሆን አብደል አዚዝ ቦህ ዋና ዳኛ፣ ዩሴፍ ሞሀመድ መሐመድ እና ብራሂም ሳሊም ረዳት እንዲሁን ሞሳ ዲያው አራተኛ ዳኛ ሆነው መመደባቸው ታውቋል።