ሪፖርት | ነብሮቹ በመጀመሪያው ጨዋታ ድል ተቀዳጅተዋል

የውድድር ዓመቱ መክፈቻ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሄኖክ አርፊጮ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል።

በበርከት ያሉ ጥፋቶች እና እነሱን ተከትለው በሚነፉ ፊሽካዎች ታጅቦ በተካሄደው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ የነብሮቹ ብልጫ የታየበት ነበር። በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአንፃራዊነት የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል። ከዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሱት ምዓም አናብስቶችም ከተቀዛቀዘው አጀማመር አገግመው ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም በቅብብል ስህተቶች እና ዘገም ባለው ሽግግር ምክንያት የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በ8ኛው ደቂቃም ከቆመ ኳስ የተሻማችው ኳስ በመቐለ ሳጥን ውስጥ በእጅ መነካትዋን ተከትሎ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሄኖክ አርፊጮ በማስቆጠር ነብሮቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ነብሮቹ ከግቡ መቆጠር በኋላም ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከነዚህም ኢዮብ ዓለማየሁ በመቐለ ተጫዋቾች ስህተት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ በጥሩ ሁኔታ ያመከናት ኳስ እና መለሰ ሚሻሞ ከርቀት የሞከራት ኳስ ይጠቀሳሉ።

በአጋማሹ ምንም እንኳ ኳስን የመቆጣጠር ውስን እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በአጨዋወቱ ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት መቐለዎች ከሳጥን ውጭ በተሞከሩ ሙከራዎች ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ከእነዚህም ሰለሞን ሀብቴ ከርቀት አክርሮ መቶት ያሬድ በጥሩ ብቃት ያወጣው እና የአብሥራ ተስፋዬ በተመሳሳይ ከርቀት ሞክሯት ለጥቂት የወጣችው ኳስ ይጠቀሳሉ።

በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ለስህተቶች የተጋለጠ እና ደካማ የመከላከል አደረጃጀት የነበራቸው
መቐለ 70 እንደርታዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የምዓም አናብስት ሙሉ ብልጫ የታየበት ነበር። በአጋማሹም በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበረው የነብሮቹ አማካይ አስጨናቂ ጸጋዬ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ የጨዋታውን መልክ ቀይሮታል።

ይህን ተከትሎም የቁጥር ብልጫ ያገኙት መቐለዎች ሙሉ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በጎል ዕድል ፈጠራ እና በሶስተኛው የሜዳ ክፍል የነበራቸው ድክመት ጥቂት የግብ ዕድሎች እንዲፈጥሩ አስገድዷቸዋል። በአጋማሹ በአመዛኙ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም የአብሥራ ተስፋዬ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከሞከራት የግብ ዕድል ውጭ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ጫና መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ሀዲያዎች በመልሶ ማጥቃት ሦስት ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም በግሉ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ተመስገን ብርሃኑ የሞከራቸው ኳሶች የግብ መጠኑን ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። ተጫዋቹ ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ መቷት ቋሚውን ታካ የወጣችው ኳስ እና ሶፎንያስ ሰይፈ ያዳናት ኳስ ከሙከራዎቹ ይጠቀሳሉ።

30 ጥፋቶች፣ 5 የቢጫ ካርድ፣ 1 ቀይ ካርድ እና 1 ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኘ ግብ ያስመለከተን የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታም በነብሮቹ አሸናፊነት ተገባዷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሀሳባቸውን የገለፁት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጨዋታ በድል መወጣታቸው ጥሩ ስሜት እንደሰጣቸው በመግለፅ ጨዋታ ከባድ እንደነበር ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም የሰራናቸው ስህተቶች ጨዋታው በጫና እንድንጨርስ አስገድዶናል ካሉ በኋላ በጨዋታው ያበከኗቸው የግብ ዕድሎች ተጋጣሚን እንዳነሳሳ ተናግረው በጨዋታውም እስከ ሶስት ግቦች የማስቆጠር ዕድል እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።
የመቐለ 70 እንደርታው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በበኩላቸው ያቀዱት የጨዋታ መንገድ ለመተግበር እንደሞከሩ በመጥቀስ የተከላካይ መስመራቸው ደካማ እንደነበር እና ብዙ ሙከራዎች እንዲሞከሩባቸው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አሰልጣኙ ጨምረውም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል በቁጥር ማነሳቸው ለማጥቃት ክፍሉ መሳሳት አንድ ምክንያት እንደነበር አንስተዋል።