ሪፖርት | ብርቱ ፉክክር በነበረው ጨዋታ ድሬዳዋዎች አሸናፊ ሆነዋል

ምሽቱን በተደረገው እና ማራኪ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ በሁለቱ አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ጎሎች አዞዎቹን 2ለ1 ረተዋል።

የዓመቱ ሁለተኛ ሆኖ በተመዘገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በክረምቱ ካደረጓቸው ዝውውሮች ድሬዳዋ ከተማ ሰባት አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው አራቱን በቋሚ አሰላለፍ አካትተዋል። በቅርቡ ሕይወታቸው ላለፈው የቀድሞው ዳኛ እና ኮሚሽነር ሲያምረኝ ዳኜ የሕሊና ጸሎት ከተደረገ በኋላ ጀምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ከዕለቱ ዳኛ ሃይማኖት አዳነ ፊሽካ አንስቶ ድሬዳዋ ከተማዎች ከራሳቸው የኋላ ክፍል በምቾት በሚያደርጓቸው ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በተለይ ወደ ግራ አዘንብለው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ስንመለከት አርባምንጭ ከተማዎች በአንፃሩ በይበልጥ ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ ሆኖ አህመድ ሁሴንን የሚፈልጉ ኳሶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲሁም ድሬዳዋዎች ጥለው የሚሄዱትን ክፍት ቦታ በተንጠልጣይ መልኩ በሚጣሉ ኳሶች ጥቃትን መሰንዘርን መርጠው ተንቀሳቅሰዋል።

የሚንሸራሸሩ ኳሶች በርከት ብለው በብዛት በተስተዋሉበት ጨዋታ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራን ከጎል ጋር 30ኛው ደቂቃ ላይ መመልከት ስንችል ጨዋታውን በመቆጣጠር የተዋጣላቸው ብርቱካናማዎቹ በአጫጭር ቅብብል ቻርለስ ሙሴጌ ያስጀመራትን ኳስን ከአብዱሰላም ጋር ተቀባብሎ የሰጠውን መሐመድኑር ወደ ግብ መቶ በአርባምንጭ ተከላካዮች በሁለት አጋጣሚ ተጨራርፋ የደረሰችውን ኳስ ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ መረቡ ላይ አሳርፏታል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ባሉት ደቂቃዎች ጨዋታው መጠነኛ መቀዛቀዞች ያሳየን ቢመስልም ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች አርባምንጭ ከተማዎች መጠቀም ቢያልሙም የፊት ተሰላፊ ተጫዋቾቻቸው ብኩንነት ገዝፎ ተንፀባርቋል። 40ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አማካዩ መስዑድ መሐመድ ጠንከር ያለ ሙከራን አድርጎ የግብ ዘቡ እድሪስ አጎጆጎ ከተቆጣጠራት በኋላ አጋማሹ ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ተመሳሳይ አቀራረብን ነገር ግን በሂደት የሚቀያየር አጨዋወትን በቡድኖቹ በኩል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ መነሻነት መታዘብ ችለናል። ወደ ጨዋታ ለመመለስ በሽግግር አጨዋወት የአህመድን ሁሴን እንቅስቃሴ ለመጠቀም የዳዱት አዞዎቹ 47ኛው ደቂቃ ላይ ከእንዳልካቸው መስፍን መሐል ለመሐል አጥቂው የደረሰውን ኳስ በሚያስቆጭ መልኩ ወደ ውጪ ሰዷታል። መሪነታቸውን ከማስጠበቅ ይልቅ ማጥቃት ላይ በይበልጥ ተሳትፎ ማድረግን የመረጡት ብርቱካናማዎቹ ከግራ በጥልቀት በሚሻገሩ ኳሶች ለመጫወት የመረጡበትን መንገድ ማስተዋል ችለናል።

ጨዋታው 66ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከአማካይ ክፍሉ ጣጣውን የጨረሰ ኳስን ያገኘው አህመድ ሁሴን አሁንም ከግብ ጠባቂው አብዩ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም በወጣቱ የግብ ዘብ ተመክቶበታል። ጨዋታው ቀጥሎ በድሬዳዋ በኩል 70ኛው ደቂቃ ሙኸዲን ሙሳ ወደ ቀኝ የሰጠውን ጀሚል ነፃ ሆኖ ያገኘውን ኳስ መጠቀም ካልቻለበት ደቂቃ በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች አዞዎቹ አህመድን የሚፈልጉ ኳሶች በይበልጥ መጠቀማቸው እንደቀጠሉ 80ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል። እንዳልካቸው ከግራ በኩል አሾልኮ የሰጠውን አህመድ ሁሴን እየነዳ ወደ ሳጥን ገብቶ በማስቆጠር ቡድኑን 1ለ1 አድርጓል።

ወደ አቻነት ከተሸጋገሩ በኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት ፈጥነው የተመለሱት ድሬዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል አቡበከር ሻሚል ወደ ግራ የሰጠውን ቻርለስ ሙሴጌ ኳሷን ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት ሲያሻግር መሐመድኑር ናስር ከካሌብ በየነ ጋር ታግሎ አስቆጥሮ ድሬዳዋን መሪ ሲያደርግ በዚህች ጎል ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የገባው የአዞዎቹ አምበል አበበ ጥላሁን በቀይ ካርድ በቀጥታ ከሜዳ ተወግዷል። የጨዋታው ግለት ከፍ እያለ በመጣባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች አርባምንጮች በአህመድ ሁሴን ድሬዳዋዎች በመሐመድኑር ናስር ያለቀላቸው ዕድሎች ቢያገኙም ጨዋታው በመጨረሻም በድሬዳዋ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የአርባምንጩ አሰልጣኝ በረከት ደሙ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ጨዋታ እንደነበር እና ተጋጣሚያቸው በደጋፊ ፊት በመጫወቱ በራስ መተማመን እንደታየበት ገልፀው በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ በሁለተኛ አርባ አምስት ደግሞ ቡድናቸው የተሻለ እንደነበር ተናግረዋል። የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው የአቻነት ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በቡድናቸው መረበሽ እንደነበር ጠቁመው ወርዶ የሚመጣ ቡድን ጠንካራ መሆኑን እንዲሁም በጨዋታው በመጀመሪያ አርባ አምስት የተጋጣሚን መከላከል ሰብሮ ለመግባት ከብዷቸው መታየቱን እና ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ግን ተጋጣሚያቸው ክፍት እንደነበር አክለዋል።