አሳ አጥማጆቹ ከነዓን ማርክነህን ለማስፈረም ተስማምተዋል።
በመስከረም 3 ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በጦሩ ቤት ለመቆየት ውሉን አራዝሞ የነበረው አማካዩ ከነዓን ማርክነህ የሊቢያውን አል መዲና ለመቀላቀል መስማማቱን ክለቡ በይፋዊ ገጹ ገለጸ።
ከአዳማ ከተማ መነሻውን ካደረገ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከእግር ኳሱ ማህበረሰብ ጋር መተዋወቅ የቻለው የአማካይ እና የመስመር አጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ቁመታሙ ተጫዋች ከነዓን ማርክነህ በአዳማ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ከነበረው የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ህይወቱ በኋላ ወደ ሊቢያ የእግር ኳስ ህይወቱን ለመቀጠል እንደተስማማ ክለቡ ይፋ አድርጓል።
ከነዓን ማርክነህን ያስፈረመው አል መዲና የተባለው በሙሉ ስሙ አል መዲና የስፖርት ፣ ባህል እና ማህበረሰብ የተሰኘው ክለብ ሲሆን በሊቢያ ፕሪምየር ሊግ ሦስት ጊዜያት ያህል ሻምፒዮን ሆኗል። ክለቡ በተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀ ሲሆን አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊውን ከነዓን ማርክነህን የስብስቡ ስድስተኛው የሌላ ሀገር ዜግነት ያለው ተጫዋችም ለማድረግ መስማማቱን ታውቋል ።
ከዚህ ቀደም በሰርቢያ የሙከራ ቆይታ የነበረው ከነዓን ወደ ሊቢያው ክለብ ለመቀላቀል መስማማቱን ተከትሎ በአልሃሊ ትሪፓሊ ቆይታ ከነበረው አማካዩ ሽመልስ በቀለ ቀጥሎ ሁለተኛው በሊቢያ ሊግ ላይ የተጫወተ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ተቃርቧል።