የጦሩ የሜዳ ላይ መሪዎች ታውቀዋል

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት መቻሎች ዛሬ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ አምበሎቻቸውን አሳውቀዋል።

ባለፈው የውድድር ዓመት እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ ለዋንጫ የተፎካከሩት እና ቡድናቸውን ለማጠናከር የነባሮች ውል በማራዘም እና አዳዲስ ተጫዋቾች በማስፈረም የቆዩት መቻሎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታ ከማከናወናቸው በፊት አምበሎቻቸውን አሳውቀዋል።

በዚህም መሰረት በቡድኑ የረዥም ዓመት ቆይታ ያለውና በሁለት አጋጣሚዎች ክለቡን ማገልገል የቻለው አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ተቀዳሚው አምበል ሲሆን እንደ ምንይሉ ሁሉ በተመሳሳይ በሁለት አጋጣሚዎች ክለቡን ለረዥም ዓመታት ያገለገለው አማካዩ በኃይሉ ግርማ ደግሞ ሁለተኛ አምበል መሆኑን ሰምተናል።

በዛሬው ዕለት ሰራተኞቹን በመግጠም የውድድር ዓመቱን የሚጀምሩት መቻሎች እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም ጠንካራ ተፎካካሪዎች ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።