በወልቂጤ ከተማ ጉዳይ አዲስ ነገር ተሰምቷል

ወልቂጤ ከተማ የዛሬውን ጨዋታ የማድረጉ ነገር አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እየታገለ የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ለማድረግ ሰዓታት የቀራቸው ወልቂጤዎች ሌላ ከባድ ፈተና ከፊታቸው ተደቅኗል ፤ ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ወልቂጤ ከተማ የሚጠበቅበትን አስገዳጅ መስፈርት ሙሉ ለሙሉ ባለሟሟላቱ የክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ እስካሁን አለማግኘቱ ታውቋል።

ትናንት በተወካያቸው አማካኝነት ከጨዋታው አንድ ቀን አስቀድሞ የሚካሄደው የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ላይ የክለቡ አባላት የተገኙ መሆናቸውን ያረጋገጥን ሲሆን አሁን ላይ ጨዋታው ሊካሄድ አራት ሰዓት ቢቀሩትም አዳዲስ ያዘዋወሯቸውን ተጫዋች ዝውውር በፌደሬሽኑ በኩል አሁን ድረስ ማፀደቅ አልቻሉም።

ለሊግ አክስዮን ማህበሩም የሚጫወቱ ውላቸው የፀደቀላቸው ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ከፌዴሬሽኑ እስካሁን አለመላኩንም እንዲሁ ያወቅን ሲሆን ነገሩን ከባድ ያደረገባቸው ደግሞ እስከ ትናንት የስራ መዝጊያ ሰዓት ድረስ የሚጠበቅባቸውን ነገሮች አለማሟላታቸው እና ዛሬ ቅዳሜ ደግሞ ባለው ግማሽ የስራ ቀን ምንም ዓይነት የተለየ ነገር አለመፈፀማቸውን ባደረግነው ማጣራት ሰምተናል።

አሁን ባለው ሁኔታ በቀሩት ሰዓታቶች የተለየ ተዓምር ካልተፈጠረ በቀር የዛሬውን ጨዋታ የማድረጋቸው ነገር የመነመነ ይመስላል ፤ ይህን ተከትሎ የሊጉን የመጀመርያ ጨዋታቸውን በፎርፌ ይጀምሩ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

ባሉት ቀሪ ጊዜያት በዚህ ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል