የጎልደን ቡት አካዳሚ ከሀዋሳ ከተማ ሁለት የስፖርት ተቋማትን ጋር በጋራ አብሮ ለመስራት ተስማምቷል።
ትውልዱ በሀዋሳ ከተማ ሲሆን በልጅነቱ ወደ ሀገረ አሜሪካ በማምራት በእግር ኳስ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን በመውሰድ በአሁኑ ሰዓት በሚኖርበት አሜሪካ ጎልደን ቡት የሚል በታዳጊዎች ላይ የሚሰራ የእግር ኳስ ማሰልጠኛን በመክፈት በርካታ ተጫዋቾች በማሰልጠን ላይ ይገኛል።
ከቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች የተወለደው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ወጣት አሰልጣኝ ንጉስ ሠለሞን ከቤተሰቦቹ ጋር ኑሮውን ከሀገር ውጪ በማድረጉ ባካበተው በቂ እውቀት ሀገሩን ማገልገል የሚፈልገው ንጉስ ከማሰልጠኛ ማዕከሉ ባለፈ የአስቶን ቪላው ሊዩን ቢይሊ ፣ የኤቨርተኑ ኦሪዮል ማንጋላ የመሳሰሉ የተለያዩ ስመጥር ተጫዋቾች የግል አሰልጣኛቸው በመሆን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በሀገራችን ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ተግባራትን በመፈፀም ላይ ይገኛል።
አሰልጣኞ ንጉስ ሰለሞን ወደ ትውልድ ከተማው ሀዋሳ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመምጣት የታዳጊዎችን ዘመናዊ ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የተለያዩ ውድድሮችን በማዘጋጀት እና የተለያዩ ድጋፎችን ከማበርከት ባለፈ በቀጣይ ስራዎችን በተሻለ መንገድ መስራት እንዲችል ከሀዋሳ ከተማ ባህል ፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ጋር እንዲሁም ከሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ፌድሬሽን ጋር በሴንትራል ሆቴል የጋራ ስምምነት ፈፅመዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይም የሀዋሳ ከተማ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ መቅደስ ሁሪሶን ጨምሮ የሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ፌድሬሽን አመራሮች እና አሰልጣኝ ንጉስ ሠለሞን በተገኙበት ስምምነቱ ተፈፅሟል።
“ተወልጄ ያደኩበትን አካባቢ በመሆኑ በእግር ኳሱ የተለዩ እና ጥሩ ነገሮች ለማበርከት ተዘጋጅቻለሁ ይህንንም ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ” ሲል በዕለቱ ንጉስ ሰለሞን ተናግሯል።
ለአምስት ዓመታት የሚዘልቀው የዛሬው ስምምነት አሰልጣኙ በቀጣይ ለታዳጊዎች የተሻለ የስልጠና እንዲሁም የተሻሉ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ለዚህም ይረዳው ዘንድ በከተማው ያሉ ምቹ ማዘውተሪያዎችን እንዲጠቀም የሚያስችለው እንደሚሆን ተገልጿል።