ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ዓመቱን በድል ጀምረዋል

ባህር ዳር ከተማ በፍጹም ዓለሙ ብቸኛ ግብ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 1ለ0 አሸንፏል።

በዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ መሪነት ምሽት 1 ሰዓት ሲል በተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል መጠነኛ ብልጫ የወሰዱት የጣና ሞገዶቹ ነበሩ። በተለይም አቤል ማሙሽ በተከላካዮች ስህተት ያገኛትን ኳስ መቶ በረከት አማረ ያዳናት ኳስ የተሻለች ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች። ባህር ዳሮች ከተጠቀሰው ሙከራ ውጭም በፍፁም ዓለሙ አማካኝነት ከቆመ ኳስ እና ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ሁለት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል።

ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ኳሶች ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ 24ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በቀኝ መስመር ላይ ሆኖ ከፍሬው ሰለሞን ኳስ የተቀበለው ወንድወሰን በለጠ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው የሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ የነበረው ፍጹም ዓለሙ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮታል። ወልዋሎዎች በአንጻሩ በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ካደረገት ሙከራ ውጭ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።


42ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ከሳጥን ወጥቶ በግንባሩ በመግጨት በትክክል ያላራቀውን ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሳ እጅግ ደካማ በሆነ ሙከራ ወርቃማውን የግብ ዕድል ሲያባክነው  በቀሪዎቹ ደቂቃዎች መጠነኛ ፉክክር ተደርጎ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በሁለቱም በኩል በርካታ የተጫዋች ቅያሪዎች ቢደረጉም 81ኛው ደቂቃ ላይ በባህር ዳር ከተማ በኩል ወንድወሰን በለጠ ከፍሬው ሰለሞን በተሻገረለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በኃይል ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ሞክሮት ካልተጠቀመበት ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች ሳይደረጉ ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል ፤ ይህም ውጤት መጋቢት 4 2012 ከሜዳቸው ውጪ ከወላይታ ድቻ ጋር ያለ ግብ ከተለያዩ በኋላ 1652 ቀናትን አሳልፈው ወደ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሱት ወልዋሎዎች በመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸው ያስተናገዱት ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚፈልጉትን እንቅስቃሴ እንዳላገኙ እና ተጫዋቾቻቸው አላስፈላጊ ረጃጅም ኳሶች ሲጠቀሙ እንደነበር እንዲሁም ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዳዩ ጠቅሰው ተጋጣሚያቸውን ባህር ዳር ከተማም እንደጠበቁት ጠንካራ እንዳልነበር ሀሳባቸውን ሲሰጡ የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው ለፍጹም ዓለሙ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው እሱ ላስቆጠረው ጎል የሌሎች ተጫዋቾችን ተሳትፎም በመጠቆም በማሸነፍ ውስጥም ብዙ ክፍተቶችን እንዳዩ እና ያንንም ማስተካከል እንዳለባቸው ገልጸዋል።