ሪፖርት |  የጦና ንቦቹ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምረዋል

ጥሩ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ አዲስ አዳጊውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ለ2 አሸንፏል።

10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግ በኤሌክትሪኮች በኩል 30ኛው ደቂቃ ላይ በሴኮንዶች ልዩነት ፍቃዱ ዓለሙ በተመሳሳይ መንገድ ከሽመክት ጉግሳ በተሻገሩለት ኳሶች ሙከራዎችን አድርጎ የመጀመሪያው በግብ ጠበቂው ቢኒያም ገነቱ ሲያዝ ሁለተኛውን ናትናኤል ናሴሮ ተደርቦ አስወጥቶበታል።

ጨዋታው 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወላይታ ድቻዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ያሬድ ዳርዛ በግራ መስመር ከተከላካይ ጋር ታግሎ በማሸነፍ እየገፋ ወደ ሳጥን የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ አሻግሮት ጌቱ ባፋ ለማቋረጥ ሲጥር ዕድለኛ ሳይሆን ቀርቶ ከግብ ጠባቂው ኪሩቤል ኃይሌ ጋር ባለመግባባታቸው ኳሱ የራሱ መረብ ላይ አርፏል።

ከዕረፍት መልስ የጦና ንቦቹ ከፍተኛ ብልጫ ወስደው ጨዋታውን ቢጀምሩም ጎል በማስቆጠሩ የተሳካላቸው ግን ኤሌክትሪኮች ነበሩ። 55ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ያልተጠበቀ ሩጫ ያደረገው ሐብታሙ ሸዋለም ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ያመቻቸውን ኳስ ያገኘው ኢዮብ ገብረማርያም በግሩም አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

የአቻነት ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተረጋጋ ሂደት የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። ፍጹም ግርማ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተስፋዬ መላኩ ከጠባብ አንግል ኳሱን በግንባር በመግጨት አስቆጥሮታል።


በመጨረሻ ደቂቃዎች ግለቱ እየጨመረ በሄደበት ጨዋታ 84ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አምበል ሽመክት ጉግሣ ዳኛው ላይ ቅሬታ ሲያቀርብ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል ፤ ሆኖም ተጫዋቹ በ3 ሴኮንዶች ቅጽበት ባደረገው ንግግር ዋና ዳኛው ዳንኤል ግርማይ በቀጥታ ቀይ ካርድ አስወጥተውታል።

ሆኖም በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት መሳይ ሰለሞን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ተገልብጦ መረቡ ላይ በማሳረፍ የጦና ንቦቹን ጎል ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 5 ደቂቃዎች ውስጥ 2ኛው ደቂቃ ላይ የጦና ንቦቹ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው በኤሌክትሪክ ተከላካዮች መዘናጋት ያለቀለት የግብ ዕድል አግኝቶ እየገፋ በወሰደው ኳስ ግብ ጠባቂውን አታልሎ ለማለፍ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ኪሩቤል አቋርጦበት ሳይሳካለት ቀርቶ ሲያባክነው 90+5ኛው ደቂቃ ላይ በኤሌክትሪክ በኩል ተቀይሮ የገባው አቤል ሀብታሙ ከአብዱላዚዝ አማን በተቀበለው ኳስ ጎል አስቆጥሮ ውጤቱን አጥብቦታል። ሆኖም ግን ጨዋታው በወላይታ ድቻ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ እንደነበሩ ጠቁመው እንደየተጋጣሚያቸው የሚለያይ አሰላለፍ እና የጨዋታ መንገድ እንደሚከተሉ ሲናገሩ ጎሎች የተቆጠሩት በአዳዲስ ፈራሚዎች መሆኑ ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ራሳቸው በሠሯቸው ቀላል ስህተቶች ጎሎችን እንዳስተናገዱ ጠቁመው የተሻለ የሚሉትን ተጫዋች ገበያው ላይ ካገኙ ማስፈረም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።