የስሑል ሽረ አምበሎች ታውቀዋል

የአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት አምበሎች ታውቀዋል።

በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ስሑል ሽረዎች ከሰዓታት በኋላ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ጨዋታ ከማከናወናቸው በፊት አምበሎቻቸውን አሳውቀውናል። በዚህ መሰረት የክለቡ ሁለተኛ ቡድን ውጤት የሆነው እና ከዓመታት በኋላ ወደ አሳዳጊው የተመለሰው የመሃል ተከላካዩ ነፃነት ገብረመድኅን የቡድኑ የመጀመሪያ አምበል መሆኑ ሲታወቅ ከድሬዳዋ ቡድኑን የተቀላቀለው ኤልያስ አሕመድ እና በተመሳሳይ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከወልቂጤ ከተማ ስሑል ሽረን የተቀላቀለው ሙሉዓለም መስፍን የቡድኑ አምበሎች ሆነው ተመርጠዋል።

ከስሑል ሽረ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ከዚህ ቀደም ከ2005 ጀምሮ እስከ 2012 ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት እና በቴክኒካል ዳይሬክተርነት ያገለገለው ወጣቱ በረከት ገብረመድኅን አዲሱ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሆኖ ተሹሟል።