ሪፖርት | ስሑል ሽረ ወደ ሊጉ ከሦስት ጎል እና ሦስት ነጥብ ጋር መመለሱን አብሥሯል

አምስት ግቦችን በተመለከትንበት ጨዋታ ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው ስሑል ሽረ አዳማ ከተማን 3ለ2 በመርታት ዓመቱን በድል ጀምሯል።

ድሬዳዋ ከምትታወቅበት ፀሐያማ ዐየር ነፋሻማ ሆና ባስተናገደችው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኳስን በተዝናኖት ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ከሚያደርጉት ቅብብል በኋላ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ቶሎ በመድረስ በሰንጣቂ የመጨረሻ ኳሶች አማካኝነት ማጥቃቱ ላይ በይበልጥ ብልጫን ወስደው መታየት የቻሉት አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ ሃያ አምስት ያህል ደቂቃዎች ባሳዩት ብልጫም የመሪነት ግብን አግኝተዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ ከአሸናፊ የደረሰውን ኳስ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን እየነዳ የገባው ቢኒያም ዐይተን ወደ ግራ አጋድሎ ለተገኘው አድናን ረሻድ ሰጥቶት አማካዩ ወደ ግብ ሲመታ ካሜሮናዊው ግብ ጠባቂ ሞይስ ፓዎቲ ቢመልሰውም ነቢል ኑሪ የተመለሰችውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ አዳማን መሪ አድርጓል።

ጎል አስቆጥረው መሪ ከሆኑ በኋላ ጥንቃቄን መርጠው ለመንቀሳቀስ ከዳዱት አዳማ ከተማዎች በተቃራኒው ቀስ በቀስ ከቆሙ አልያም በቀኝ የሜዳው ክፍል የአሰጋኸኝ ጴጥሮስን እንቅስቃሴ ተጠቅመው አቻ ለመሆን ጥረት ያደረጉት ሽረዎች በተደጋጋሚ ካደረጉት የማጥቃት ጫና በኋላ ጎል ማስቆጠር ሲችሉ በ27ኛው ደቂቃ በጥሩ የእግር ስራ ከፋሲል ጋር ተጫውቶ ከመስመር ወደ ውስጥ አሰጋኸኝ ያሻገረውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ ጨርፎት ከጀርባው የነበረው ዩጋንዳዊው አጥቂ አሌክስ ኪታታ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦታል።

ሁለት ጎሎችን ካስመለከተን በኋላ ወረድ ያሉ አቀራረቦች በርክተው በቀጠሉበት ጨዋታ ስሑል ሽረዎች የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው በማድረግ በጨዋታው ልዩነት ለመፍጠር ቢጥሩም ከሰላሳ ደቂቃዎች መልስ ጥራቱን የጠበቀ ሙከራን ሳንመለከትበት አጋማሹ ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ አዳማ  ከተማ የሁለት ተጫዋች ቅያሪን አድርገው ሲመለሱ ኃይለሚካኤል አደፍርስ እና አድናን ረሻድ ወጥተው ቻላቸው መንበሩ እና ሙሴ ካቤላን ተክተዋል። ተመጣጣኝ የሚመስል መልክ ሜዳ ላይ እየተስተዋለ በቀጠለው ጨዋታ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አዳማዎች በቅያሪ ተጫዋቹ ቻላቸው መንበሩ የግራ ክፍል በማጋደል በጥልቅ አጨዋወት ለመጫወት በሚጥሩበት ወቅት በተወሰነ መልኩ ጥሩነታቸው ጎልቶ ቢታይም የመጨረሻው ሜዳ ላይ ቢኒያም ዐይተን ኳሶችን በጥልቀት ወደ መሐል እየመጣ ለመቀበል በመገደዱ በቀላሉ የማጥቃት ደመነፍሳቸው መቀዛቀዙ ሙከራዎችን እንዳያደርጉ ዕክል እንደሆነባቸው መታዘብ ችለናል።

ጥንቃቄ ላይ አተኩረው ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በመልሶ ማጥቃት በፍጥነት ተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲገኙ የታዩት ሽሬዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሪነት በድጋሚ ተመልሰዋል። ጃፈር ከመሐል ወደ ግራ የሰጠውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት ሲያሻግር የአዳማ ተከላካዮች የቦታ አያያዝ ስህተት ታክሎበት አላዛር አድማሱ ተቀይሮ እንደገባ ያገኛትን ኳስ መረብ ላይ አስቀምጧታል።

ጨዋታው ሲቀጥል አዳማ ከተማዎች ሙሉ በሙሉ ብልጫውን ወስደው በተደጋጋሚ ሳጥን አካባቢ ቶሎ ቶሎ ሲደርሱ ቢስተዋልም በጥብቅ መከላከል አጥራቸውን ያስጠበቁት ሽረዎችን ሰብረው መግባት ተስኗቸው በነበረው ወቅት ይባስ በ85ኛ ደቂቃ ለማጥቃት ጥለው የሄዱትን የሜዳ ክፍል በመልሶ ማጥቃት ፋሲል አስማማው ብቻውን ያገኛትን ኳስ ለማስጣል ወደ ሳጥን የደረሰው ፍቅሩ ዓለማየሁ ከመጠነኛ ትግል በኋላ በፋሲል ላይ ሳጥን ውስጥ የሠራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ኤልያስ አህመድ ከመረብ አሳርፎ የሽረን መሪነት ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል። መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ እንደቀሩ አሜ መሐመድ ላይ ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል ሳጥን ውስጥ የሠራውን ጥፋት ተንተርሶ የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ቢኒያም ዐይተን ቢያስቆጥርም አዳማን ከሽንፈት መታደግ ሳይችል ጨዋታው በስሑል ሽረ 3ለ2 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ብዙ የቤት ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀው በዝግጅት ወቅት የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጋቸው እና ቡድናቸውም ጫና ውስጥ እንደነበር ጠቁመው በሂደት በጨዋታ እየተገነባ እንደሚሄድ እና ብዙ ክፍተትም እንዳለባቸው ማጥቃቱም ላይ ደካማ እንደሆኑ እንዲሁም ቡድኑ በጉዞ ወቅት በነበረ ሂደት በተጫዋቾች ላይ ድካም እንደታየም አክለዋል። የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በበኩላቸው ማሸነፍ ቦታ እና ጊዜ እንደማይመርጥ ጠቅሰው ለሚቀጥለው ጨዋታ ማሸነፋቸው ተነሳሽነታቸውን ከፍ እንደሚያደርግ እንዲሁም ተጋጣሚያቸው አዳማም እንደጠበቁት ሆኖ አለመቅረቡን በንግግራቸው ጠቁመዋል።