በወልቂጤ ከተማ ጉዳይ ምን አዲስ ነገር አለ?

የሊጉን የመጀመርያ ጨዋታውን በፎርፌ የተሸነፈው ወልቂጤ ከተማ በተመለከተ ምን አዲስ ነገር አለ ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ማጣራት አድርጋለች።

ወልቂጤ ከተማ የሚጠበቅበትን አስገዳጅ መስፈርት ሙሉ ለሙሉ ባለሟሟላቱ የክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ አለማግኘታቸውን ተከትሎ ያሳለፍነው እሁድ ከመቻል ጋር ሊያደርጉት የነበረው የሊጉ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ ሳያከናውኑ በፎርፌ መሸነፋቸው ይታወሳል።

የሊጉ አክስዮን ማህበር የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በወልቂጤ ላይ ከሰጠው ፎርፌ ባሻገር የሚወስደው የዲሲፒሊን ቅጣት እንደተጠበቀ ሆኖ ነገ ረቡዕ ምሽት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ወይስ በተመሳሳይ ፎርፌ ይሰጣሉ የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ሆኗል።

የወልቂጤ ከተማ ክለብ አመራሮች ከትናንት ጀምሮ ባሉት የስራ ቀናቶች የክለብ ላይሰንሲግ ፍቃዱን ለማግኘት የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ለሟሟላት ምን እየሰሩ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ የክለቡን ፕሬዝደንት አቶ ሞሳን አናግራ እንዳገኘችው ምላሽ ከሆነ “የሚጠበቅብንን አሟልተን ለመጨረስ የከፈልናቸው ክፍያዎች አሉ የቀረው ከፊፋ ጋር የተያያዙትንም ቢሆን ውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙን ትንሽ ችግሮች አሉ ይህንንም ለመቅረፍ እየሰራን ነው።ዛሬ ሁሉን ነገር አጠናቀን ፈቃዱን እናገኛለን ብለን እናስባለን ብለዋል።”

ከእግርኳሱ የበላይ አካል በኩል ወልቂጤ መስፈርቱን ለሟሟላት እየሄደ ያለበትን ርቀት ለማወቅ ባደረግነው ማጣራት አንዳንድ ክፍያዎችን እየፈፀሙ እንደሚገኝ እና ሌሎች ያልተከፈሉ ክፍያዎችን ለመፈፀም በቀሩት የስራ ቀናት ይበልጡኑ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖሩ መረጃዎችን ተከታትለን የምናቀርብ ሲሆን ሠራተኞቹ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ነገ ረቡዕ መስከረም 15 ቀን ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ከወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ከንግድ ባንክ ጋር ጨዋታቸውን እንዲሚያደርጉ አስቀድሞ የወጣው መርሐ-ግብር ያሳያል።