የቻን ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ቀን ታወቀ

ከወራት በኋላ እንደሚጀምር የሚጠበቀው የቻን ውድድር በሦስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የጋራ አዘጋጅነት የሚከናወን ሲሆን ውድድሩ የሚጀመርበት እንዲሁም የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ጊዜ ይፋ ሆኗል።


የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን ብቻ የሚያሳትፉ ብሔራዊ ቡድኖች የሚወዳደሩበት የቻን ውድድር ከ2009 ጀምሮ ሲከናወን የነበረ ሲሆን ባለንበት ወር 2024 መደረግ የነበረበት ግን ወደ 2025 የተዘዋወረው ውድድር በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሆኑት ኬኒያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ አዘጋጅነት የሚከወን ሲሆን ዋናው ውድድር የሚደረግበት ቀንም ሆነ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ የሚከወኑበት ጊዜ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

በዚህም ውድድሩ ከጥር 25 እስከ የካቲት 20 ድረስ በሦስቱ የቀንዱ ሀገራት አዘጋጅነት የሚከወን ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎች ከጥቅምት 15-17/ ጥቅምት 22-24 ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከታሕሳስ 11-13/ ታሕሳስ 18-20 የሚከናወኑ ይሆናል።

በየዞኑ (ዋፉ ኤ፣ ዋፉ ቢ፣ ዩናፍ፣ ዩኒፋክ እና ኮሳፋ) ሦስት ሦስት ብሔራዊ ቡድኖች በውድድሩ የሚሳተፉ ሲሆን በሴካፋ ዞን የሚገኙት የውድድሩ አዘጋጆች ኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ በቀጥታ ሲያልፉ በማጣሪያ አንድ ተጨማሪ የቀጠናው ብሔራዊ ቡድን ተካቶ በአጠቃላይ በ19 ቡድኖች መካከል ውድድሩ የሚደረግ ይሆናል።

ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ካፍ ለአባል ሀገራቱ በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ የምድብ ጨዋታዎች ላይ የቻን ውድድር መጠነኛ ጥላ ስለሚያጠላ የቀን ሽግሽግ እንዳደረገ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በተመለከተ ዋልያዎቹ በመጨረሻው የቻን ውድድር ስለተሳተፉ በመጀመሪያው ዙር የቅድመ ማጣሪያ የማይሳተፉ ሲሆን በሁለተኛው ዙር አንድ የደርሶ መልስ ጨዋታ ብቻ ከውነው ወደ ውድድሩ የሚወስዳቸውን ትኬት ማግኘት የሚችሉ ይሆናል።