ወጣቷ የመስመር ተጫዋች የታንዛኒያውን ክለብ ለመቀላቀል ወደ ስፍራው ተጉዛለች።
ከአርባምንጭ የጀመረው የእግር ኳስ ህይወቷ በኋላም በአሰልጣኝ ማህደር እንየው ስር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አራት የስልጠና ዘመናትን በማሳለፍ በክለብ ደረጃ በመቻል እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታን ያደረገችው የመስመር የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቿ አረጋሽ ካልሳ ከሀገር ውጭ ለመጫወት ተቃርባለች።
ያለፉትን ሦስት የውድድር ዘመናት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተሳኩ ዓመታቶች የነበራት እና ከክለቡም ጋር የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ ከሳምንታት በፊትም ከክለቧ ጋር የሴካፋ ዞን የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያሳካችው የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አረጋሽ ካልሳ የታንዛኒያውን ያንጋ አፍሪካንስ የሴቶች ቡድንን በአንድ ዓመት ውል ለመቀላቀል መቃረቧን እና ይህን ሂደት ለማጠናቀቅ ወደ ስፍራው ማቅናቷን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እስከ መስከረም 30 2017 ድረስ የሚቆይ ውል ያላት ተጫዋቿ በሁለት ሺህ ዶላር ወርሃዊ ደሞዝ እንዲሁም ለዝውውሩ ደግሞ ሦስት ሺህ ዶላርን ወጪ ተደርጎባት ወደ አዲሱ ክለቧ ታመራለች ተብሎ ይጠበቃል።
ከሳምንታት በፊት ለያንጋ አፍሪካንስ በይፋ ፊርማቸውን ካኖሩት የቀድሞው የንግድ ባንክ አማካይ ንቦኝ የን እና አጥቂዋ አሪያት ኦዶንግ ቀጥሎ በክለቡ የምትጫወት ሦስተኛዋ ኢትዮጵያዊ መሆኗም ዕርግጥ የሆነ መስሏል።