ብሩክ ማርቆስ ከግብፅ ክለብ ጥያቄ ቀርቦለታል

እጅግ ፈጣን አድገትን እያሳየ የሚገኘው አማካዩ ብሩክ ማርቆስ ከግብፅ ክለብ ጥያቄ እንዳቀረበለት ሶከር ኢትዮጵያ መረጃውን አግኝታለች።

ከሁለት ዓመት በፊት በሆሳዕና ከተማ በክረምት በማደረገው የያሆዴ ዋንጫ ላይ ጥሩ ሲንቀሳስ በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ዕይታ ውስጥ ገብቶ ሀድያ ሆሳዕናን ከተቀላቀለ በኋላ ያለፉትን ዓመታት በቡድኑ ውስጥ ቁልፍ ሚናን ሲወጣ የነበረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ብሩክ ማርቆስ በግብፅ ክለብ እንደተፈለገ ወኪሉ አዛርያስ ተስፋፂዮን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

የተጫዋች ብሩክ ፈላጊ የሆነው ክለብ የግብፁ ኤል ጉውና መሆኑ ታውቋል ፤ ኤል ጉውና ብሩክን ለማስፈረም አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ተጫዋቹ ወደ ግብፅ የፊታችን አርብ እንዲመጣ የአውሮፕላን ትኬት እና የቪዛ ጉዳይ መጨረሱን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አሁን የሚጠበቀው የብሩክ ህጋዊ ባለቤት የሆነው ሀድያ ሆሳዕና ፍቃደኝነት ብቻ ነው ፤ ምክንያቱም ብሩክ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የሚያቆየው የአንድ ዓመት ቀሪ ኮንትራት ያለው በመሆኑ ነው።

ክለቡ በዚህ ጉዳይ ያለውን አቋም ለማወቅ ያናገርናቸው የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አባተ ሲናገሩ “ ጥያቄው ቀድሞ ቢመጣ ኖሮ ለተመስገን እዳደረግነው መላክ እንችል ነበር። አሁን ሊጉ ተጀምሯል በዚህ ሰዓት ብሩክ ቢሄድ እርሱን ለመተካት የሚያስችል ተጫዋች ማምጣት ከባድ ነው። አሰልጣኙም ብሩክን መልቀቅ ቡድኑን ማፍረስ ስለሚሆን እንዲቆይለት ጠይቆናል። ስለሆነም ብሩክን ለመልቀቅ እንቸገራለን ብለዋል።”

የግብፁ ክለብ ኤል ጉውና የተመሰረተው ከ21 ዓመታት በፊት ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዋናው ሊግ ያደገው በ2008/09 ነበር ፤ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም በሊጉ በ39 ነጥብ 12ተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ ለአንድ ዓመት በክለቡ ተጫውቶ ማሳለፉ አይዘነጋም።