ሁለተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራል። በነገው ዕለት ጨዋታውን የማያከናውን ከሆነ ከውድድሩ የሚታገደው ወልቂጤ ከተማ ጨምሮ የሌሎች ቡድኖችን መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድቷል።
ኢትዮጵያ መድን ከ አርባምንጭ ከተማ
በመጀመርያው ሳምንት አራፊ የነበረው ኢትዮጵያ መድን እና አዲስ አዳጊው አርባምንጭ ከተማ የሚያደርጉት የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ መርሃግብር ሁለቱም ቡድኖች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥብ ለማስመዝገብ ይፋለሙበታል።
በአመዛዡ ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ የገነቡት ጠንካራ ቡድን ይዘው ወደ ውድድር የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች በተጠናቀቀው ዓመት የመጨረሻ ሳምንታት ጠንካራ የማጥቃት እና የመከላከል አቅማቸው ካስቀጠሉ ቢያንስ ከወገቡ በላይ ሆነው የሚያጠናቅቁበት ዕድል የሰፋ ነው።
በተለይም ፈጣን ሽግግር ላይ የተመሰረተው እና ውጤታማው የፊት ጥምረታቸው አሁንም የሚጠበቅ የቡድኑ ጥንካሬ ነው። በክረምቱ አማካዩ ዳዊት ተፈራን ጨምሮ በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን ያስፈረመው ቡድኑ ከባለፈው የውድድር ዓመት ቋሚ አሰላለፉ ውስን ለውጦች ብቻ አድርጎ ይገባል ተብሎም ይገመታል።
ከአንድ ዓመት በኋላ በተመለሱበት ሊግ በድሬዳዋ ከተማ የሁለት ለአንድ የተሸነፉት አርባምንጭ ከተማዎች ምንም እንኳ ሽንፈት ቢያስተናግዱም በሁሉም ረገድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። አዞዎቹ በውስን መልኩ ማስተካከያዎች ከሚፈልገው የመከላከል አደረጃጀታቸው ውጭ መልካም እንቅስቃሴ ባሳዩበት ጨዋታ የነበራቸው ስል የፊት መስመር ጥምረት የቡድኑ ዋና ጥንካሬ ሆኖ አልፏል፤ በተለይም የታታሪው አጥቂ አሕመድ ሁሴን ምርጥ ብቃት የቡድኑን የፊት መስመር አስፈሪነት አላብሶታል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል ሚሊዮን ሠለሞን ካለፈው አመት የተላለፈ ቅጣት አለን ካይዋ ጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ፤ በአንፃሩ አዞዎቹ በመጨረሻው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ተከላካዩ አበበ ጥላሁንን በቅጣት፤ ጋናዊው ተከላካይ ስቴፈን ባዱ እና ናይጄሪያዊው አማካይ ቻርለስ ሪባኑ ደግሞ በወረቀት ጉዳዮች በጨዋታው አያሰልፉም።
ወልቂጤ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የመካሄዱ ነገር እርግጥ ያልሆነው የጨዋታ ሳምንቱ ሁለተኛ ጨዋታ አንድ ሰዓት ላይ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታ የሚያከናውኑት ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ መርሃግብር እስካሁን ድረስ የመካሄዱ ነገር እርግጥ ባይሆንም በመጀመርያው የጨዋታ ሳምንት ለመቻል ፎርፌ የሰጡት ሰራተኞቹ በቀሪ ሰዓታት የሚጠበቅባቸው ውዝፍ ዕዳዎች ካገባደዱ ጨዋታው ይከናወናል ተብሎ ይገመታል።
ሰራተኞቹ በፊፋ ከተከሰሱባቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው የኮትዴቭዋራዊ ግብ ጠባቂ ውዝፍ ዕዳ የከፈሉ ሲሆን የኬንያዊው ተጫዋች ውዝፍ ዕዳም ለመከፈል በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ቡድኑ በቀሩት ሰዓታት የኬንያዊው ተጫዋች ጨምሮ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ውዝፍ ዕዳ የሚያገባድዱ ከሆነ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ክለቡ የሚጠበቅበትን ነገሮች የማያገባድድ ከሆነና የነገው ጨዋታ የማያከናውን ከሆነውም በህጉ መሰረት ከውድድሩ የሚታገድም ይሆናል።
በአህጉራዊ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሻምፕዮኖቹ ንግድ ባንኮች ከያንግ አፍሪካንስ አስከፊ ሽንፈት በኋላ የባለፈው ዓመት የአሸናፊነት ጉዟቸው ለመቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። በአመዛዡ የሀገሪቱን ዋና ሊግ ያሸነፈው ጠንካራው ስብስባቸውን ይዘው የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ዘንድሮም ለዋንጫ ከሚታጩት ቀዳሚ ቡድኖች ውስጥ ናቸው። ሻምፕዮኖቹ ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነው ስብስባቸው ይዘው የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጨዋታ ለማከናወን በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።