የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታውን የሚያደርግበት ሀገር ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ጋር የሚያደርጋቸውን ሦስተኛ እና አራተኛ የምድብ ጨዋታዎች በኮትዲቯር እንደሚያደርግ ፌደሬሽኑ ይፋ አድርጓል። ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ታንዛኒያ ላይ አከናውኖ ከታንዛኒያ ጋር ያለ ጎል አቻ እንዲሁም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁለት ለባዶ የተረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ከጊኒ ጋር የሚያደርገውን የሜዳ ላይ ጨዋታውን በኮትዲቫር አቢጃን ከተማ በሚገኘው ስታድ ደ ኢቢምፔ ስቴድየም የሚያከናውን ይሆናል።
በምድቡ ሦስተኛ ጨዋታ ጥቅምት 1 ከሜዳቸው ውጭ ጊኒን የሚገጥሙት ዋልያዎቹ ጊኒ ጨዋታዋን ለማድረግ ባስመዘገበችው ስታድ ኮናን ባኒ ስቴድየም የሚጫወቱ ሲሆን ከአራት ቀናት በኋላ የሚካሄደው የምድቡ አራተኛ ጨዋታም አቢጃን በሚገኘው ስታድ ደ ኢቢምፔ ያከናውናሉ።
የመጀመርያዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች በታንዛንያ ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ምድቡን ዲምክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስትመራው ታንዛኒያ፣ ኢትዮጵያ እና ጊኒ ተከታታይ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ።