መረጃዎች | 6ኛ የጨዋታ ቀን

የሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለትን የተመለከቱ መረጃዎቹ በተከታዩ ጽሑፍ ቀርበዋል።

ፋሲል ከነማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ከሆኑት መርሐግብሮች አንዱ የሆነው ይህ መርሐግብር በመጀመሪያ የጨዋታ ዕለት ድል ያስመዘገቡትን ፋሲል ከነማዎችን የውድድር ዘመኑን በሽንፈት ከጀመሩት መቐለ 70 እንደርታዎች ያገናኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን በተረቱበት ጨዋታ ሁለቱንም ግቦች ከቆሙ ኳሶች ማስቆጠር የቻሉት ፋሲሎች በነገው ጨዋታ ለመቐለዎች ከቆሙ ኳስ ከፍተኛ አደጋን እንደሚደቅኑ ይጠበቃል ፤ በአንፃሩ ምንም እንኳን ሽንፈት ያስተናግዱ እንጂ በእንቅስቃሴ ረገድ መጥፎ ያልነበሩት መቐለ 70 እንደርታዎች በነገው ጨዋታ ውጤት ይዘው ለመውጣት ከወገብ በላይ ያላቸው ቁመና ላይ እርምት መውሰድ ይኖርባቸዋል።

በፋሲል ከነማ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች በአዲስ የቡድን ግንባታ መንገድ የተገነባው ስብስብ በመጀመሪያ ጨዋታ ያሳዩት ያልሸነፍ ባይነት ስሜት በአውንታዊነት የሚነሳ ሲሆን በአንፃሩ በርከት ባሉ አዲስ ተጫዋቾች የተገነባው መቐለ 70 እንደርታም ይህን የአሸናፊነት ስሜትን ዳግም በተመለሱበት ሊግ ውስጥ በፍጥነት ማግኘትን ይሻሉ።

ከፍተኛ ፉክክር እንደሚደረግበት በሚጠበቀው የሁለቱ ቡድኖች የነገ መርሐግብር በፋሲል ከነማ በኩል ጌታነህ ከበደ አሁንም ጉዳት ላይ ከመገኘቱ በስተቀር የተቀረው ስብስብ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ሲታወቅ መቐለ 70 እንደርታዎች በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የወጣው ተመስገን በጅሮንድ ጨምሮ መናፍ ዐወል እና ኪሩቤል ኃይሉ በጉዳት ምክንያት የማያሰልፉ ሲሆን የሥራ ፍቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ያሉት አዳዲስ ፈራሚዎቹ አልፋ ኖህ ሴሳይ እና ኮፊ ኮርድዚም የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። ጋናዊው አማካይ ቤንጃሚን አፉቲ የሥራ ፍቃዱን ማግኘቱ እና ያሬድ ከበደ ከመጠነኛ ጉዳት አገግሞ ለጨዋታው መድረሱም ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ደግሞ የወድድር ዘመኑን የመጀመሪያ መርሐግብራቸውን የሚያደርጉትን ኢትዮጵያ ቡናዎችን ዓመቱን በሽንፈት ከጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።

በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከዓምናው ስብስባቸው በብዙ የተለወጠ እና በአዳዲስ ፊቶች የተሞላ ስብስብን ይዘው የውድድር ዘመኑን የሚጀምሩ ይሆናል ፤ በወጣቶች የተሞላው ስብስብ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሊጉ እንዴት ይቀርባል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

በአንጻሩ በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት በወላይታ ድቻ ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተከታታይ ሽንፈቶችን ላለማስተናገድ በተለይ በቀላሉ ግቦችን ሲያስተናግድ የተመለከትነው የቡድኑ የመከላከል መዋቅር ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ የግድ የሚላቸው ይሆናል።

የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በሊጉ ለማድረግ እየተዘጋጁ በሚገኙት በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሽመክት ጉግሳን በቅጣት የሚያጡት ሲሆን ተከላካዩ ገለታ ኃይሉ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ መሰለፉ ሲያጠራጥር ጋናዊው ግብ ጠባቂ አብዱላሂ እንድሪስ የወረቀቱ ጉዳይ እስከ ዛሬ ያለለቀ ሲሆን ነገ የሚያልቅለት ከሆነ ለጨዋታው ዝግጁ ይሆናል።