ከፍተኛ ሊግ| ሶሎዳ ዓድዋዎች በርከት ያሉ ዝውውሮች አገባደዋል

በአሰልጣኝ አሸናፊ አማረ የሚመሩት ሶሎዳ ዓድዋዎች የነባር ተጫዋቾች ውል ሲያራዝሙ በርከት ያሉ ተጫዋቾችንም አስፈርመዋል።

ቀደም ብለው አሸናፊ አማረን በመቅጠር የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት ሶሎዳ ዓድዋዎች የስምንት ነባር ተጫዋቾችን ውል ሲያድሱ በተጨማሪም በርከት ያሉ ዝውውሮችን አገባደዋል።በቡድኑ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት የተስማሙት የቀድሞው የመቐለ እና ሽሬ ተጫዋቾች የነበረው ሙሉጌታ አንዶም ፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በመቐለ ተጫውቶ ያሳለፈው ዳንኤል አድሀኖም ፣ ግብ ጠባቂዎቹ ፊልሞን ገ/እግዚአብሔር እና ካፒታል ተስፋይ እንዲሁም የመስመር ተከላካዩ መሀሪ አድሀኖም አጥቂው ስለሺ ዘሪሁን፤ አማካዮቹ ቢንያም ተሻለ እና ኤርምያስ ብርሀነ በቡድኑ ለመቆየት ውላቸውን አራዝመዋል።

ወደ ክለቡ የተቀላቀሉ አዳዲስ ፈራሚዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና ፣ ደደቢት ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ ተጫውቶ ያሳለፈው ከድር ሳልሕ፤ ባለፉት ዓመታት በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታ የነበረው ተስፈኛው አማካይ አሌክሳንደር ገብረሕይወት ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተጫወተው አጥቂው በረከት ብርሃኑ፤ በአክሱም ከተማ፣ ቡራዩ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ የተጫወተው የግራ መስመር ተከላካዩ ዮሐንስ ዓፈራ፤ በነቀምት ከተማ እና ቢሾፍቱ ከተማ ቆይታ የነበረው አማካዩ ሰይድ ሬድዋን፤ ከዚህ ቀደም በአክሱም ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ የተጫወተው ተከላካዩ ሰላማዊ ገብረሥላሴ እንዲሁም የቀድሞ የሀላባ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ተከላካይ ሚኪያስ ዓለማየሁ  እና በትግራይ ዋንጫ የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የነበረው የቀድሞ የዋልታ ፖሊስ ትግራይ አጥቂ ዳንኤል ወርቀልዑል ቡድኑን የተቀላቀሉ አዳዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል።