ሪፖርት | ፋሲል እና መቐለ ነጥብ ተጋርተዋል

ከአራት ዓመታት በኋላ በሊጉ ዳግም የተገናኙት ፋሲል እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

ፋሲል ከነማዎች በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ድል ካደረገው ስብሰባቸው ምንም ለውጥ ያላደረጉ ሲሆን በአንፃሩ በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት መቐለ 70 እንደርታዎች በኩል የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደረጎ በዚህም መናፍ ዐወል ፣ ዮናስ ግርማይ ፣ ኪሩቤል ሐይሉ እና ተመስገን በጅሮንድ አርፈው በምትካቸው ሸሪፍ መሐመድ ፣ ዘረሰናይ ብርሀነ ፣ ቤንጃሚን ኮቴ እና አሸናፊ ሀፍቱ ተክተዋቸው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከአራት ዓመታት በኋላ በፕሪምየር ሊጉ ዳግም የተገናኙን ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ፈጣን የማጥቃት አጀማመር የታየበት ነበር። አፄዎቹ ያስጀመሩትን ኳስ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ያገኘው ቃልኪዳን ዘላለም በጥልቀት ይዞ ገብቶ በሞከራት እና ሶፎኒያስ ሰይፈ ባመከናት አጋጣሚ ጨዋታው ሲጀምር ኳስን በመቆጣጠር ሁለቱን መስመሮች በመጠቀሞ ተጫዋቾቻቸው በሚያደርጓቸው ንክኪዎች የማጥቃት የተሻለ ፍላጎት ያሳዩት ፋሲሎች ብልጫን ወስደው ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን በድግግሞሽ መድረስ ቢችሉም ወጥ ያልነበሩ ቅብብሎቻቸው ሲመክኑ ተስተውሏል።

7ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ቃልኪዳን ዘላለም መቶ ሶፎኒያስ ሰይፈ የመከታት እና 20ኛው ደቂቃ በጥሩ አንድ ሁለት ከማርቲን ኪዛ ያለቀለት ኳስን ያገኘው ቃልኪዳን ነፃ ሆኖ ያገኛትን ዕድል ጥንካሬ አልባ በሆነ ምቱ ለሶፎኒያስን አሳቅፎታል።

ወደ ጨዋታ ለመግባት ተቸግረው የታዩት እና ረጅሙን ደቂቃ በተጋጣሚያቸው በእጅጉ የተበለጡት መቐለዎች ከየአብስራ ተስፋዬ እግር በሚነሱ እና ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ማጥቃትን መርጠው ቢንቀሳቀሱም የፋሲል የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ተቸግረው መመልከት ችለናል።

በ28ኛው ደቂቃ መቐለዎች ፋሲሎች ለማጥቃት ነቅለው መውጣታቸውን ተከትለው ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ፤ ያሬድ ብርሀኑ ራሱ ያስጀመራት ኳስ ወደ ግራ መስመር ይዞ አምርቶ ከጀርባው ለነበረው ቦና ሰጥቶት ተጫዋቹም ወደ ውስጥ ሲያሻግር በዮናታን ተጨርፋ የደረሰችውን ኳስ ያሬድ ብርሀኑ ከአራት ዓመታት በኋላ በተመለሰበት ፕሪምየር ሊግ ግብ አድርጓታል በዚህም ግብ አጋማሹ በመቐለ የበላይነት ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀጠለ በሚመስል መልኩ የፋሲል ከነማ የበላይነትን እያሳየን በቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ መቐለዎች በመረጡት የጥንቃቄ አጨዋወት በተጋጣሚያቸው በተደጋጋሚ ለጥቃት ቢዳረጉም በመልሶ ማጥቃት በሚጫወቱበት ሰዓት ግን አደገኛ መልክ ነበራቸው ለዚህም ማሳያው 58ኛው ደቂቃ ያሬድ ብርሀኑ ለአሸናፊ ሀፍቱ ሰጥቶት ሳጥን ውስጥ የመታትን ኳስ በግቡ ቀኝ ቋሚ በኩል ኳሷ ታካ ወጥታለች።

እንደነበራቸው ብልጫ የተጋጣሚያቸውን አጥር ሰብሮ ለመግባት የተቸገሩት ፋሲሎች በሌላኛው ሜዳ ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው 68ኛው ደቂቃ አሸናፊ ሀፍቱ በተንጠልጣይ መልኩ የሰጠውን ኳስ ጎል አስቆጣሪው ያሬድ ሞክሯት ወደ ውጪ ኳሷ መውጣት ችላለች።

ብልጫውን ቢይዙም ግብ ለማግኘት ተቸግረው የቆዩት ፋሲሎች በመጨረሻም 66ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ከግቡ ትይዩ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ጋናዊው ተከላካይ ሸሪፍ መሐመድ ቢኒያም ላንቃሞ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠችዋን የቅጣት ምት ራሱ ቢኒያም እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ለውጧት ጨዋታው ወደ አቻነት ተለውጧል።

ጨዋታው ወደ መጠናቀቂቃው ሲቃረብ በመጠነኛ ፉክክር ሁለቱም ቡድኖች ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም ጨዋታው በ1ለ1 ውጤት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በእንቅስቃሴ ደረጃ መጥፎ እንዳልነበሩ እና በመጀመሪያው አጋማሽ ጎል ማስናገዳቸው ወደ ጥድፊያ እንደመራቸው ጠቁመው በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ በመናገር በማጥቃት ሽግግራቸው ወቅት የተከላካይ መስመራቸው ላይ ክፍተት ይፈጠር እንደነበር ሀሳባቸውን ሲሰጡ የመቐለ 70 እንደርታ አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በበኩላቸው በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሚፈልጉት መንገድ መጫወታቸውን ገልጸው ካለፈው የሀዲያ ጨዋታቸው አንጻር የተሻለ እንቅስቃሴ ማየታቸውን በመጠቆም ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ቢጠቀሙ ማሸነፍ ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል።