የሁለተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ሦስት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን በተከታዩ ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ስሑል ሽረ
የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸውን ድል ያደረጉ ሁለትን ቡድኖች የሚያገናኘው መርሃግብር ረፋድ 3፡30 ላይ ይደረጋል።
ሲዳማ ቡናን በደርቢ ጨዋታ ድል ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች በነገው ዕለትም ወደ ሊጉ ዳግም የተመለሱት ስሑል ሽረዎች ላይ ተከታታይ ድልን ለማስመዝገብ እና አጀማመራቸውን የበለጠ የተሳካ ለማድረግ አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጥብቅ መከላከል እና በፈጣን ሽግግሮች አስደናቂ የመክፈቻ ሳምንትን ያሳለፉት ሀዋሳዎች ልማደኛው ዓሊ ሱሌይማንን ዘንድሮም ዋነኛ የማጥቂያ መንገዳቸው እንደሆነ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ኃይቆቹ በነገው ጨዋታም ይህንኑ የጨዋታ መንገድ ማስቀጠላቸው የማይቀር እንደሆነ ቢጠበቅም በቀላሉ የሚፈጥሯቸውን ዕድሎች ከመጠቀም አኳያ የታየባቸውን ውስንነቶች ነገ አሻሽለው መቅረብ የማይችሉ ከሆነ በተጋጣሚያቸው ሊቀጡ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ከአራት የውድድር ዘመናት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት ስሑል ሽረዎች ከመጀመሪያ ድላቸው ማግስት የድል ግስጋሴያቸውን ለማስቀጥል ከሊጉ ባለ ልምዱ ክለብ ፈተና ያስተናግዳሉ ተብሎ ይታሰባል።
ከአዳማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ በፍጥነት ወደ ጨዋታ ለመግባት ተቸግረው የተመለከትን ሲሆን
ነገም በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ በፈጣን የአጥቂ ክፍል የሚመራው ሀዋሳ ከተማ ምህረት የለሽ በትሩን ሊያሳርፍባቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
ነገር ግን ቡድኑ በሽግግሮች በተለይም አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በሚገኝበት የቀኝ መስመር በኩል ሲያጠቃ አስፈሪ መልክን የተላበሰ በመሆኑ አንዳች ነገርን ሊፈጥር እንደሚችል መጠበቅ ግድ ይላል ይህንን ለማድረግ ግን ከጠንካራው የሀዋሳ የተከላካይ ክፍል ጋር ለመፋለም የሚገደድም ይሆናል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል አዲሱ ፈራሚ ዮሴፍ ታረቀኝን ጨምሮ በመጀመሪያ የሊጉ መርሃግብር ተሰልፈው የነበሩት እንየው ካሳሁን እና አብዱልባሲጥ ከማል በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ በስሑል ሽረዎች በኩል ደግሞ በመጀመሪያው ጨዋታ ጎል ያስቆጠሩት አሌክስ ኪታታ እና አላዛር አድማሱ መሰለፋቸው አጠራጣሪ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ
በፕሪምየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎቸው በተጋጣሚዎቻቸው ሽንፈት ያስተናገዱትን ሁለቱን ቡድኖችን የሚያገናኘው መርሃግብር 10 ሰዓት ሲል ይጀምራል።
በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ መሪነት አዳዲስ ፊቶችን ይዞ ብቅ ባለበት የባለፈው ሳምንት ጨዋታ እንደ ቡድን የማጥቃት ፍላጎታቸው ከፍ ያለ ስለመሆኑ ያስተዋልንባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን ለመሸመት ከሌላኛው ነጥብ ፈላጊ ወልዋሎ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ይታሰባል።
በመከላከሉ ላይ ከነበረባቸው ውስን ክፍተቶች በተጨማሪ ማጥቃት ላይ ቡድኑ ፍላጎቱ ከፍ ያለ በመሆኑ በተለይ በፋሲሉ ጨዋታ አጥቂው ፍፁም ጥላሁን የሚያገኛቸውን ኳሶች ሲያመክን የታየ ሲሆን በነገው ጨዋታ ላይ ግን ዕርምትን መውሰድ ካልቻሉ የቤት ስራቸውን ከፍ ያለ እንዳይሆን ያሰጋል።
ወደ ሊጉ በተመለሱበት የመጀመሪያ የጨዋታ ተሳትፎአቸውን በሽንፈት የጀመሩት ወልዋሎዎች ከፍተኛ መሻሻሎችን እያሰቡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይፈለማሉ።
ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ረጃጅም ኳስን ምርጫቸው ያደረጉት እና በመከላከሉም የተደራጀ አወቃቀር ያልነበረው ቡድኑ ነገ ብዙ ዕቅዶችን ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ዳዋ ሆቴሳ ካደረጋት ብቸኛ ሙከራ ውጪ ግልፅ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው የታዩት ወልዋሎዎች እንደ መከላከሉ ሁሉ የፊት መስመሩን ማስተካከል ካልቻለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ሊቸገር እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም።
አዲሶቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈራሚዎች ዩጋንዳዊው ተከላካይ ጊፍት ፍሬድ እና ቶጓዊው አጥቂ ሳሚዮ ታቻታኮራ በወረቀት ጉዳዮች አለማለቅ የተነሳ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ የተቀረው የቡድኑ ስብስብ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። ወልዋሎዎች በአንፃሩ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ ስብስብን ይዘው ይቀርባሉ።
ባህርዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ
በድል እና በሽንፈት ሊጉን የጀመሩ ሁለት ክለቦች ምሽት 1 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ የማሳረጊያ መርሐግብር ይሆናል።
በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመሩት ባህርዳር ከተማዎች የመጀመሪያ ድላቸውን ነገም ለማስቀጠል ይፋለማሉ።
አማካይ ክፍል ላይ ብልጫን ወስዶ ወደ አጥቂው ወንድወሰን በለጠ በሚደርሱ ኳሶች በወልዋሎው ጨዋታ መጫወትን የመረጠው ቡድኑ ነገም የፍሬው እና ፍፁምን ጥሩ ጥምረት ተጠቅሞ የሚንቀሳቀስ ከሆነ መከላከሉ ላይ ግልፅ ክፍተት ያለባቸው አዳማ ከተማ ላይ ውጤት ይዞ ሊወጣ እንደሚችል ይገመታል።
እንደ አሰልጣኙ አብዲ ቡሊ ገለፃ ከሆነ ሦስት ልምምዶችን ሳያደርጉ በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆነው በአንደኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በስሑል ሽረ ለመሸነፍ የተገደዱት አዳማዎች ሦስት ነጥብን እያሰቡ ነገ እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።
በወጣት ተጫዋቾቹ እየታገዘ ዘንድሮ ስል ሊሆን እንደሚችል በጨዋታ ሳምንቱ በጥቂቱ ያስመለከተን ቡድኑ ከፈጠራ አኳያ የነበረበትን ትልቅ ችግር ካላረመ እና በመከላከሉ ደግሞ የሚታይበትን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ካላረመ በፈጣኑ የባህርዳር የአጥቂ ክፍል መፈተኑ አይቀሬ ነው።
ባህርዳር ከተማ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሲሆኑ አዳማ ከተማዎች ግን አምበላቸው ዳንኤል ደምሱን በጉዳት ሳቢያ የማሰለፋቸው ነገር ግን አጠራጣሪ ሆኗል።