የመዲናይቱን አንጋፋ ክለቦች ያገናኘው የምሽቱ መርሃግብር በአቻ ውጤት ተገባዷል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች አዲስ ፈራሚዎቹ ዳንላድ ኢብራሂም፣ ኮንኮኒ ሐፋዝ እና ዲቫይን ዋቹክዋ አካተው ጨዋታውን ሲጀምሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በወላይታ ድቻ ሽንፈት ካስተናገደ ቋሚ አሰላለፍ ኪሩቤል ኃይሌ፣ ገለታ ኃይሉ እና ሽመክት ጉግሳ በአሸብር ተስፋዬ፣ ያሬድ የማነ እና አሸናፊ ጥሩነህ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ እና ፉክክር በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ውጤታማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባይታይም ከመስመር ወደ ሳጥን በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሞከሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአንፃራዊነት የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል፤ ከነዚህም ያሬድ የማነ አሻምቶት ፍቃዱ ዓለሙ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ያዳነው ኳስ እና አሸናፊ ጥሩነህ ከርቀት አክርሮ የሞክረው ኳስ ይጠቀሳሉ።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ በሂደት የተሻሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎችም ግብ ለማግኝት ተቃርበው ነበር። አማኑኤል አድማሱ ከቀኝ መስመር በኩል አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው በአግባቡ ያልተቆጣጠረው ኳስ አንተነህ ተፈራ አግኝቶ መቶት አምበሉ ጌታሁን ባፋ በጥሩ ብቃት ያወጣው ኳስም ቡናማዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ነበር፤ ዋሳዋ ጂኦፍሪ በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ከቆመ ኳስ ያደረገው ሙከራም ሌላ የሚጠቀስ ነበር።
በአንፃራዊነት ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የግብ ሙከራዎች ያስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ ሁለተም ቡድኖች በተመሳሳይ በፈጣን ሽግግር እና በረዣዥም ኳሶች ቀጥተኛ አጨዋወት ቢከተሉም የተፈጠሩት የግብ ዕድሎች ግን ወደ ግብነት አልተቀሩም።
ሆኖም ኢትዮጵያ ቡናዎች በኮንኮኒ ሐፋዝ እና ኤርምያስ ሹምብዛ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ በፍቃዱ አለሙ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም በኤሌክትሪክ በኩል ፍቃዱ ዓለሙ እዮብ ገብረማሪያም ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ጎልነት ያልቀየረው ኳስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና በኩል ዲቫይን ዋችኩዋ በግሩም ሁኔታ ወደ ሳጥን አሻግሮት ኮንኮኒ ሐፋዝ መቶት ቋሚውን ገጭቶ የተመለሰው ሙከራ በሁለቱም በኩል ለግብነት የቀረቡ ነበሩ።
የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በአቻ ውጤት መገባደዱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥባቸውን አስመዝግበዋል ፤ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሀሳባቸው የሰጡት የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የጨዋታው እንቅስቃሴ መጥፎ እንዳልነበር ጠቅሰው የመከላከል አድረጃጀታቸው ከባለፈው ጨዋታ እንደተሻሻለ በመጥቀስ በቀጣይም የማጥቃት አጨዋወቱ ለማሻሻል እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ቀጥለው ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ቡድናቸው ጥሩ መፎካከር የሚችል ተስፋ የሚጣልበት ቡድን እንደሆነ በመጥቀስ ቡድናቸው ከዕረፍት በፊት ጉጉቶች እንደታዩበት ከዕረፍት በኋላ ግን ዕድሎች አለመጠቀማቸው እንደክፍተት አንስተዋል።