በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ በነበረው የረፋድ ጨዋታ ስሁል ሽረዎች በእጃቸው ገብቶ የነበረውን ሙሉ ሦስት ነጥብ በመጨረሻ ደቂቃ የመከላከል ስህተት አጥተዋል።
ሀዋሳ ከተማዎች ሲዳማ ቡናን ከረታው የመጀመሪያ 11 ተመራጮቻቸው ውስጥ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች አቤነዘር ዮሀንስ እና ሲሳይ ጋቾ በአብዱልባሲጥ ከማል እና እንየው ካሳሁንን ተክተው ሲገቡ ስሁል ሽረዎች ደግሞ አዳማን ከረታው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ማድረግ ችለዋል በዚህም ብርሃኑ አዳሙ እና አሌክስ ኪታታን አስወጥተው በምትካቸው መሀመድ አቡዱለጢፍ እና አላዛር አድማሱን ተጠቅመዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሀዋሳ ከተማዎች የበላይነት የተንፀባረቀበት ነበር ፤ በቀላሉ የሽረን ሳጥን ሲጎበኙ ያረፈዱት ሀዋሳ ከተማዎች በርከት ያሉ ሙከራዎችን ወደ ግብ ያደረጉም የሙከራዎቹ ጥራት ግን አመርቂ አልነበሩም በአጋማሹ በተለይ ዓሊ ሱሌይማን በ7ኛው እና 17ኛው ደቂቃ እንዲሁም አቤነዘር ዮሀንስ 25ኛው ደቂቃ ላይ ከሽረው ግብ ጠባቂ ግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ያደረጋት እና በግብ ዘቡ የተመለሰችበት ሙከራ የተሻሉ የሚባሉት ነበሩ።
በአንፃሩ ወደ ጨዋታው ለመግባት እስከ ውሃ ዕረፍት ድረስ ለመጠበቅ የተገደዱት ሽረዎች በንፅፅር በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ ምንም እንኳን ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ባያደርጉም በ30ኛው እና 44ኛው ደቂቃ ከሀዋሳ ተጫዋቾች በተነጠቁ ኳሶች መነሻነት ፋሲል አስማማው ያደረጋችው ድንቅ ሙከራዎች ሰዒድ ሀብታሙን የፈተኑ ነበሩ።
ሁለተኛው አጋማሽን በተሻለ መነቃቃት የጀመሩት ስሁል ሽረዎች በ48ኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ መሀመድ አብዱለጢፍ በአስደናቂ የግል ጥረት ረጅም ርቀት እየገፋ የሄደውን ኳስ ወደ ሳጥን ውስጥ አመቻችቶ ያቀበለው ፋሲል አስማማው ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል።
በተመሳሳይ ስሁል ሽረዎች ከአምስት ደቂቃ በኃላ መሪነታቸውን ማሳደግ የሚችሉበት ዕድል የመጀመሪያውን ግብ ላይ ተሳትፎ በነበራቸው ሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት መፍጠር ቢችሉም ፋሲል ያደረገውን ሙከራ ሰዒድ ሀብታሙ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል።
ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በማለም በርከት ያሉ አውንታዊ ለውጦችን በማድረግ ጨዋታቸውን ቢያደርጉም ሽረዎች ሳጥን ውስጥ መገኘት ቀላል አልሆነላቸውም ፤ በአጋማሹም በ68ኛው እና 72ኛው ደቂቃ እስራኤል እሸቱ እና ዓሊ ሱሌይማን ከሳጥን ውጭ ያደረጓቸው ሙከራዎች ሞይስ ፖዎቲ አድኗቸዋል።
ምን እንኳን መሪነቱን ከወሰዱ በኃላ በመጠኑም ቢሆን የማጥቃት ፍላጎታቸው ቀዝቀዝ ብለው የታዩት ስሁል ሽረዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል አስማማው በግሩም የመልሶ ማጥቃት ያገኘውን አጋጣሚ ከሰዒድ ሀብታሙ ጋር ተገናኛቶ ያደረገውን ሙከራ እንዲሁም 91ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ፋሲል ያደረጋቸውን ሙከራዎች ሰዒድ በግሩም ሁኔታ አድኖባቸዋል።
ጨዋታው በሽረዎች አሸናፊነት ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሁኔታ ሀዋሳ ከተማዎች 92ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ያሻሙትን ኳስ የሽረ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂ በፈጠሩት አለመግባባት የሽረው ግብ ጠባቂ ሞይስ ፖዎቲ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ከጨዋታው በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የስሁል ሽረው ጌታቸው ዳዊት ያገኟቸውን ዕድሎች አለመጠቀማቸው እና ሙሉ ሦስት ነጥብን አለማሳካታቸው ቅር እንዳሰኛቸው ገልፀው ዳግም ወደ ሊጉ እንደተመለሰ ቡድን በእንቅስቃሴያቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ አሁን ያላቸውን ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ለማስቀጠል እንደሚሰሩም ገልፀዋል።የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩሉ በተቃራኒ ሜዳ በቀላሉ የሚበላሹ ኳሶች ቡድናቸውን በመልሶ ማጥቃት ጫና ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ገልፀው በባለፈው ጨዋታ ያወጡት ከፍተኛ ጉልበት በዛሬው ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ ስለመፍጠሩም አንስተዋል።