ከሠራተኞቹ መውጣት በኋላ ሊጉ በምን ዓይነት መልክ ይቀጥላል?
ወልቂጤ ከተማዎች የክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ ለማግኘት ሟሟላት የሚጠበቅባቸውን አስገዳጅ መስፈርቶች ባለማጠናቀቃቸው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ፎርፌ ለመስጠት መገደዳቸውን ይታወሳል።
በዚህ መሰረት አወዳዳሪው አካል ወልቂጤ ከተማ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ፎርፌ መስጠቱን ተከትሎ በተቀመጠው የዲሲፒሊን መመርያ መሠረት የወልቂጤን ከውድድር መሰረዙን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ሶከር ኢትዮጵያም ወልቂጤ ከተማ ከውድድሩ ከወጣ በኋላ በቀጣይ ምን ይሆናል ስትል ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው አካላት ማጣራት አድርጋለች። በዚህ መሰረት በቅርቡ በውድድሩ መርሐግብር ላይ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ እና ከሦስተኛው ሳምንት በኋላ አዲስ የመርሐግብር ድልድል እንደሚኖር እንዲሁም በየሳምንቱ የነበረው አንድ ቡድን አራፊ የሚሆነው ድልድል እንደማይኖር አረጋግጠናል።
ከዚህ በተጨማሪም አንድ ቡድን ለሁለት ዙር ተመዝግቦ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር ከግማሽ በታች ተካፍሎ ቢያቋርጥ ወይም ከውድድሩ ቢወጣ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ይሰረዛሉ፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎችን ካቋረጠው ቡድን ጋር ተጋጣሚ ለሆኑ ቡድኖች ምንም ነጥብም ሆነ ግብ አይመዘገብም በሚለው ደንብ መሠረት በሁለቱም ሳምንታት የወልቂጤ ከተማ ተጋጣሚ የነበሩት መቻል እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፎርፌ ያገኙትን ውጤት እንደሚሰረዝና በሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ በወልቂጤ ከተማ ላይ የቅጣት ውሳኔ እንደሚበየን ለማወቅ ተችሏል።