ከዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ቤቱ የተመለሰው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ድሉን አስመዝግቧል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፋሲል ከነማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ አማኑኤል ኤርቦ እና ፀጋ ከድር በተገኑ ተሾመና ዳግማዊ አርአያ ተክተው ሲገቡ ወልዋሎዎችም በተመሳሳይ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ሰለሙን በርሐ፣ ታዬ ጋሻው እና ዳዋ ሆቴሳ በናሆም ኃይለማርያም፣ ሰመረ ኪዳነ ማርያም እና ቃሲም ረዛቅ ተክተው ገብተዋል።
ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በኪሩቤል ወንድሙ እና እያሱ ለገሰ የእርሰ በርስ ግጭት ምክንያት እያሱ ለገሰ አስደንጋጭ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን ጨዋታውም በሰባተኛው ደቂቃ ነበር ግብ የተስተናገደበት።
ተገኑ ተሾመ ከአማካይ ክፍል የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ አሻግሮት ፍፁም ጥላሁን በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ ያሳረፋት ጎልም ፈረሰኞቹን መሪ አድርጋለች።
ከግቧ በኋላ ለደቂቃዎች የተረጋጋ እንቅስቃሴ ማድረግ የተሳናቸው ወልዋሎዎች ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ በኪሩቤል ወንድሙ አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል።ተከላካዩ ጋዲሳ መብራቴ ከቆመ ኳስ በጥሩ ሁኔታ ያሻገራትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ነበር ያስቆጠረው።
አሰቃቂ ጉዳት፣ ሦስት ቅያሪዎች እና ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ በአቻ ውጤት ሲገባደድ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተገኑ ተሾመ በአንፃራዊነት በአጋማሹ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረገው ተጫዋች ነበር።
ተገኑ ተሾመ ከመስመር አሻምቶት አብርሀም ጌታቸው ባደረገው የመጀመርያ ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ጥቂት የማይባሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተደርገውበታል። በተለይም በተጠቀሰው ደቂቃ የሙከራዎች ብልጫ የነበራቸው ወልዋሎዎች በቡልቻ ሹራ እና ዳዊት ገብሩ ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
ሰለሞን ጌታቸው በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን አሻግሯት ዳዊት ገብሩ በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያልተጠቀመባት ዕድልም ተጠቃሽ ናት። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ብሩክ ታረቀኝ ከቆመ ኳስ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ሙከራ ቡድኑ በሁለተኛ አጋማሽ ከፈጠራቸው ዕድሎች ትጠቀሳለች፤ በ71ኛው ደቂቃም ፈረሰኞቹ በአማኑኤል ኤርቦ ግብ አማካኝነት ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አጥቂው ቶሎሳ ንጉሴ ከመዓዘን ምት ያሻማትን ኳስ በግንባር በመግጠት ነበር ግቧን ያስቆጠረው።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ቀይረው ያስገቡት ወልዋሎዎችም በቡልቻ ሹራ የግምባር ኳስ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም አብርሀም ጌታቸው እንደምንም አውጥቷታል።
ይህን ተከተትሎ ጨዋታው በፈረሰኞቹ የ2ለ1 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ያስተናገዱት ፈረሰኞቹ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ነጥባቸው ስያስመዘግቡ ወልዋሎዎች ተከታታይ ሽንፈት ለማስመዝገብ ተገደዋል።
ከጨዋታው በኋላ ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በጨዋታው መሸነፍ እንደማይገባቸው ጠቅሰው የእያሱ ለገሰ ጉዳትም ጨዋታው ላይ ተፅዕኖ እንዳደረገ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም የእያሱ ለገሰ ጉዳት ከባድ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ቀጥለው ሀሳባቸው የሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ፈልገው እንደመጡ በመጥቀስ ጨዋታውን ማሽነፋቸው ብዙ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በጨዋታ መሀል የሚታየው የወጥነት ችግር በቀጣይ እንደሚያሻሽሉም ተናግረዋል።