ሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይገባደዳል፤ ብርቱ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ የሳምንቱ መገባደጃ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
መቻል ከ ሲዳማ ቡና
በውድድር ዓመቱ ለዋንጫ ፉክክሩ ቅድመ ግምት የተሰጣቸውን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
በመጀመርያው ሳምንት ወልቂጤ ከተማን በፎርፌ ያሸነፉት መቻሎች በውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ጨዋታቸውን ያከናውናሉ ፤ ባለፈው ዓመት እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ለዋንጫ የተፎካከረው ስብስብ ላይ አዳዲስ ተጫዋቾች ጨምረው ጠንካራ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ባለፈው ዓመት በአመዛኙ የተጠቀሙበት በፈጣን ሽግግር ላይ የተመሰረተውን ውጤታማው አጨዋወታቸው ይቀይራሉ ተብሎ አይገመትም።
ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ በዝውውር መስኮቱ ያዘዋወራቸው አዳዲስ ፈራሚዎች ይጠቀማል ተብሎ ሲጠበቅ ይህን ተከትሎም ባለፈው የውድድር ዓመት ጥያቄዎች ሲነሳበት የነበረው የቡድኑ የኋላ ክፍል ላይ ለውጦች መኖራቸው አይቀሪ ነው።
በመጀመርያው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው ሲዳማዎች ከሽንፈት ለማገገም ጦሩን ይገጥማሉ ፤ በውድድር ዓመቱ በርከት ያሉ ዝውውሮች በመፈፀም ቡድናቸውን ያጠናከሩት ሲዳማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በወሰዱበት የመጨረሻው ጨዋታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች ተስተውሎባቸዋል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በነገው ዕለትም ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለመልሶ ማጥቃቶች ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል። በጨዋታው በሊጉ መክፈቻ በግሉ በርከት ያሉ ሙከራዎች በማድረግ መልካም አጀማመር ያደረገው መስፍን ታፈሰ ከተጠባዊ ተጫዋቾች አንዱ ነው።
በመቻል በኩል በኃይሉ ግርማ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከቡድኑ ጋር የማይገኝ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር በዝግጅት ላይ ያሉት ተጫዋቾች ግን ለዚህ ጨዋታ መመለሳቸው ታውቋል። ሲዳማ ቡናዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
ዓመቱን በድል የጀመሩ ሁለት ክለቦችን የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሃግብር ሌላኛው ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚገመተው ጨዋታ ነው።
በአዲሱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ስር መልካም አጀማመር አድርገው ዓመቱን በድል የጀመሩት ብርቱካናማዎቹ በተመሳሳይ በመጀመርያው ጨዋታ ካሸነፉት የጦና ንቦች ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚጥር እና በርካታ የማጥቃያ አማራጮች ያሉት ቡድን የገነቡት ድሬዳዋዎች በነገው ጨዋታ በመከላከል አደረጃጀታቸው ውስን ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሚኖርባቸው የመጨረሻው ጨዋታ ጠቋሚ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ላይ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ ቡድን እንደመግጠማቸው የሚጠብቃቸው የመከላከል ፈተና ቀላል ይሆናል ተብሎ አይገመትም። የቻርለስ ሙሴጌ እና መሐመድኑር ናስር ጥምረትም በቡድኑ የሚጠበቅ ጠንካራ ጎን ነው።
በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ዓመቱን የጀመሩት የጦና ንቦች በመርሃግብሩ ድል ከመቀዳጀት ባለፈ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለመውሰድ የሚጥር አቀራረብ የነበረው ቡድኑ በነገው ዕለት በተመሳሳይ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን እንደመግጠሙ ቀላል ፉክክር አይጠብቀውም።
ከዚህ በተጨማሪ በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ሁለት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው መልካም አጀማመር ላደረገው የብርቱካናማዎቹ የፊት ጥምረት ልዩ ዝግጅት አድርጎ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያሬድ ታደሰ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በዝግጅት የቆዩ ተጫዋቾች ግን ለነገው ጨዋታ ቡድናቸውን ተቀላቅለዋል።