የ3ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን አያገኙም

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምስል መብት ባለቤት የሆነው ሱፐር ስፖርት የ3ኛ ሳምንት የሊጉን መርሐ-ግብሮች እንደማያስተላልፍ ታውቋል።

ዘንድሮን ጨምሮ ያለፉትን አራት ዓመታት የሀገራችንን ከፍተኛው የሊግ ዕርከን ውድድር የምስል መብት የገዛው ሱፐር ስፖርት በአንድ ከተማ የሚደረገውን የሊግ ውድድር ለአድማጭ ተመልካቾች ሲያደርስ እንደነበር አይዘነጋም። ዘንድሮ የውሉ ማብቂያ ላይ የሚገኘው ተቋሙ እንዳለፉት ዓመታት ዘንድሮ ከውሉ በላይ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን እንደማያስተላልፍ የተሰማ ሲሆን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሳምንታት ግን በሙሉ ለተከታዮቹ አድርሷል።

ከዚህ በፊት ባቀረብነው ዘገባም ምናልባት የሊጉ የሁለት ሳምንታት ጨዋታዎች ብቻ እንደሚተላለፉ በጠቆምነው መሰረት ከነገ ጀምሮ የሚደረጉት የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በቴሌቪዥን ኩባንያው ሽፋን እንደማይኖራቸውና የቀጥታ ስርጭት ባለሙያዎቹ በዚህ ሰዓት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በሂደት ላይ እንደሆኑ አውቀናል።

የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተደርገው ከ15 ቀናት የብሔራዊ ቡድን እረፍት በኋላ ሊጉ በ4ኛ ሳምንት ሲመለስም የቀጥታ ስርጭቱ ይኖራል ወይስ አይኖርም የሚለው ጉዳይ እንዳልተወሰነም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።