የእያሱ ለገሠ አሁናዊ ሁኔታ?

አሰቃቂ ጉዳት ያስተናገደው የወልዋሎ ዓ/ዩ ተከላካይ እያሱ ለገሰ ወቅታዊ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማጣራት ሞክረናል።

ከትናንት በስትያ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እያደረጉ በነበሩት ጨዋታ ጅማሮ ተከላካዩ እያሱ ለገሰ ከጉልበቱ በታች ያለው የግራ እግሩ ክፍል ሁለቱም አጥንቶቹ መሰበሩን (ስብራቱ በህክምና አጠራሩ- Left Mid shaft Tibial and Fibula Fracture) ተከትሎ የህክምና ባለሙያዎች በፍጥነት በመግባት ተጫዋቹ በአንቡላስ በአፋጣኝ ቀዳዴ አጠቃላይ ሆስፒታል እንዳመራ እና ለተሻለ ህክምና ትናንት ወደ አዲስ አበባ ሊጓዝ እንደሚችል ዘገባ አቅርበን ነበር።

የክለቡ አመራሮች እያሱ በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ የሚሄድበትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልተው የአውሮፕላን ትኬት ቆርጠው በጠዋት ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ቢደርሱም “እያሱ ባለበት ሁኔታ በመደበኛ በረራ መሄድ አይችልም” የሚል ምላሽ ከአየር መንገዱ ተሰቷቸዋል።

በክለቡ ወልዋሎ ዓ/ዩ ፣ ድሬዳዋ በሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ ፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ. የጋራ ጥረት ተጫዋቹ ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ ጥረት ማድረጋቸውን የሰማን ሲሆን የእያሱ የግራ እግር መታጠፍ ባለመቻሉ በስትሬቸር ከቦይንግ አውሮፕላን ውጪ በመደበኛ አውሮፕላን መብረር እንደማይችል ከአየር መንገዱ በመገለፁ በትናንትናው ዕለት ተጫዋቹ አዲስ አበባ መግባት አልቻለም።

ምናልባት የተጎጂዎች ስትሬቸር ወደ ድሬዳዋ ከሚመጣው ቦይንግ አውሮፕላን ጋር የሚመጣበት ዕድል አነስተኛ መሆኑን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ቢሮ በመገለፁ እና ተጫዋቹ በ72 ሰዓታት ውስጥ አዲስ አበባ ደርሶ ቀዶ ጥገናውን ማድረግ ስለሚገባው የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በከተማው የሚገኝ ዘመናዊ አምቡላንስ ከከፍተኛ የህክምና ቡድን ጋር በማንቀሳቀስ በየብስ ትራንስፖርት ለሊቱን በመጓዝ አዲስአበባ በሚገኘው የስፖርት ጉዳቶች ህክምና ማዕከል ‘Dream Orthopedic and Spine Center’ በዕውቁ የስፖርት ህክምና እና የመገጣጠሚያ ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ማሞ ደቅሲሳ አማካኝነት ከቀዶ ህክምና በፊት የሚደረጉ ምርመራዎችን እያደረገ እንደሆነ ሰምተናል። ተጫዋቹም ነገ ማለዳ ቀዶ ጥገናውን እንደሚሰራ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በጉዳዩ ዙርያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤሌ አምደመስቀል በእነሱ በኩል ተጫዋቹን በተሻለ ፍጥነት ወደ አዲስ አበባ ለመውሰድ የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታ ቢያሟሉም ሊሳካ አለመቻሉን ገልፀው በቀጣይ መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሚመለከተው አካል መሰራት እንዳለበት አመላክተዋል።

ተጫዋቹን በተመለከተ ድሬዳዋ ላይ ከቀዶ-ህክምና በፊት የሚደረግ Long Leg Posterior Gutter ማለትም የተሰበረውን የአጥንት ክፍል ደግፎ የሚይዝ የጀሶ ህክምና የተደረገለት ሲሆን ከለሊቱ የመኪና ጉዞ በኋላ ያለበት የድካም ሁኔታ እና የቅድመ ምርመራ ውጤት መነሻነት በቀጣዮቹ ሰዓታት ቀዶ ጥገናውን እንደሚያደርግ ሰምተናል።