የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን የማያገኙትን የሦስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን በተከታዩ ጥንቅር እንመለከታቸዋለን።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቐለ 70 እንደርታ
የሦስተኛ ሳምንት ቀዳሚ የሆነው የሁለቱ ቡድኖች መርሐግብር ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቅ ነው።
በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ መሪነት የሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ በሽንፈት ቢጀምሩም በሁለተኛ ሳምንታቸው ግን በብዙ መሻሻሎች ድልን የተቀዳጁት ፈረሰኞቹ በነገው ዕለትም ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በወልዋሎው ጨዋታቸው በይበልጥ ለሽግግር አጨዋወት ራሳቸውን ምቹ በማድረግ በተለይ የሜዳውን ሁለት የግራ እና ቀኝ መስመሮች ተጠቅመው የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ያሳኩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነገም ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ሲጠበቅ ቡድኑ ከወገብ በላይ ካለው ጥንካሬ ባሻገር ግን በመከላከሉ ላይ እርምቶችን መውሰድ እንደሚኖርበት እያለመ መግባት ይጠበቅበታል።
ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ነጥብን ብቻ መያዝ የቻሉት መቐለ 70 እንደርታዎች ከሦስት ነጥብ ጋር በጊዜ ለመታረቅ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይገጥማሉ። በመልሶ ማጥቃት በተከታታይ ጨዋታዎች ስል እንደሆነ ያሳየን የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ስብስብ እንደሚታይበት ከፍ ያለ የማጥቃት ጥንካሬው በተቃራኒው በመከላከሉ ላይ ያለበትን የአደረጃጀት ወጥነት መቅረፍ ካልቻለ ግን በፍፁም ጥላሁን በሚመራው የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ከበድ ያለ ቅጣት ሊሰነዘርበት እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁንም የወረቀት ጉዳዮቻቸውን ማጠናቀቅ ያልቻሉትን ዩጋንዳዊውን ተከላካይ ጊፍት ፍሬድ እና ቶጓዊውን አጥቂ ሳቢዮ ታቻታኮራ ነገም የማያገኙ ሲሆን በወልዋሎ ጨዋታ በሆድ ህመም ተቀይሮ የወጣው የግብ ዘቡ ባሕሩ ነጋሽ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። ሊጉ ገና ከመጀመሩ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በጉዳት እያጡ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች በነገው ጨዋታም ተመስገን በጅሮንድ ፣ መናፍ ዐወል ፣ ኪሩቤል ኃይሉ እና አምበሉን የአብሥራ ተስፋዬን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።
ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብን እያለሙ ወደ ሜዳ የሚገቡ ቡድኖችን የሚያገናኘው መርሐግብር ምሽት ላይ ይደረጋል።
በመጀመሪያው ሳምንት አራፊ በመሆናቸው የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ብቻ ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በቡድናቸው ላይ የዝግጅት ጊዜ ማነስ እንዳለ ማንሳታቸው የሚታወስ ሲሆን ብዙ መሻሻሎችን እየፈለጉ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታሉ። የዳዊት ተፈራን እንቅስቃሴ በመጠቀም ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ትኩረት አድርጎ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የታዘብነው ቡድኑ ደካማ የሆነውን የሦስተኛ ሜዳ አጠቃቀም ማስተካከል የሚገባው ሲሆን የኳስ ቁጥጥሩ ላይ ግን በተሻለ ብልጫን መውሰድ ላይ አተኩረው የነገ ተጋጣሚያቸውን አስቸጋሪ ሊያደርጉበት እንደሚችሉ መጠቆም ያሻል።
ምንም እንኳን ሦስት ነጥብን እስከ አሁን አያግኝ እንጂ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከፍ ያለ ተነሳሽነትን ያስመለከተን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጠንካራውን የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ በመድን ላይ ዳግም ሊያስመለክተን ይችላል ተብሎ ይገመታል። ሁለቱን የማጥቂያ መስመሮች በተለይ ወደ ቀኝ ተሰላፊው ኢዮብ ገብረማርያም አዘንብሎ ሲጫወት አደገኛ መልክ የሚያሳየው የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ስብስብ ነገም የተለየ የጨዋታ አቀራረብን እያስመለከተን ለመጀመሪያ ሦስት ነጥቡ ይፋለማል።
ኢትዮጵያ መድኖች አሁንም ሚሊዮን ሠለሞንን እና ዋንጫ ቱትን በቅጣት አለን ካይዋ ፣ መሐመድ አበራ እና ያሬድ ካሳዬን ደግሞ በጉዳት አያገኙም ፤ በአርባምንጩ ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አዲስ ተስፋዬም መሰለፉ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽመክት ጉግሳን በቅጣት ገለታ ኃይሉን በጉዳት አያገኝም አዲሱ ጋናዊ ግብ ጠባቂ አብዱላሂ እንድሪስ የወረቀቱ ጉዳዮቹን እስከ አሁን ማጠናቀቅ ያልቻለ ሲሆን በነገው ዕለት ምሳ ሰዓት ድረስ የሚያጠናቅቅ ከሆነ ሊሰለፍ እንደሚችል ይጠበቃል።