የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 መቐለ 70 እንደርታ

“ጨዋታው በምንፈልገው የእግርኳስ ሂደት ሄዷል ብለን ባናምንም በዚህ ሰዓት የሚፈለገው 3 ነጥብ ስለሆነ ተጫዋቾቻችንን ለከፈሉት ዋጋ ማመስገን እፈልጋለሁ።” አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ

“ጎሎችን ማግባት እስካልቻልክ ድረስ ዋጋ መክፈልህ አይቀርም።” አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

መቐለ 70 እንደርታዎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረቱ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ – መቐለ 70 እንደርታ

ስለ ድሉ

”ከአራት ዓመት ተኩል በኋላ ነው ቡድኑ ወደ ሊጉ የተመለሰው በዚህ ምክንያት አንድ ተሸንፈናል አንድ አቻ ወጥተናል ዛሬ አሸንፈን አራት ነጥቦችን ይዘናል በዚህ አጋጣሚ ደጋፊዎቻችንን እንኳን ደስ አለን ማለት እፈልጋለሁ”።

የደጋፊዎቹ አስተዋጽኦ እንዴት ነበር?

”ከሰሜን እስከ ምስራቅ ጫፍ መጥተው ቡድኑን መደገፍ በዛ ላይ ሆቴል ተከራይቶ በተለያዩ ወጪዎች መቆየት ትልቅ መስዋዕትነት ነው። የውድድሩም ድምቀት ናቸው እና በክለቡም በተጫዋቾችም ስም ከልብ እናመሰግናለን”

ድሉ ለቀጣይ የሚፈጥረው በጎ ነገር?

”የእረፍት ሰዓት ድል ከመሆኑም አንፃር ለቀጣይ ሥራችን የተሻለ ትኩረት አድርገን በሞራል የተሻለ እንድንሰራ ያደረገናል እና በዚህ አጋጣሚ ጨዋታው እኛ በምንፈልገው የእግርኳስ ሂደት ሄዷል ብለን ባናምንም በዚህ ሰዓት የሚፈለገው 3 ነጥብ ስለሆነ ተጫዋቾቻችንን ለከፈሉት ዋጋ ማመስገን እፈልጋለሁ”

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው…

”በመጀመሪያዎቹ 15 እና 20 ደቂቃዎች ብዙ የግብ ዕድሎችን ስተናል። እየሳትክ በሄድክ ቁጥር ተጋጣሚህ በሳይኮሎጂም እየበለጠህ ይመጣል። በሁለተኛም አጋማሽም ቢሆን ጨዋታውን ተቆጣጥረን መጫወት ችለን ነበር ሆኖም ግን የጥራት ችግር ስለነበር ውጤት ማምጣት አልቻልንም። በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ግብ በመድረስ እና የግብ ዕድሎችን በመፍጥሩ በኩል ብልጫ ነበረን ግን ጎል አግብተህ እስካላሸነፍክ ድረስ በእኔ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም።”

ስለ ቡድኑ ስብስብ ጥራት …?

”ከውጪ ሚመጡ ተጫዋቾች አሉ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ያላለቀ ምናልባት ከፊት ያለንን አቅም በልምድም በጥራትም ከፍ ያደርጉናል ብለን እናስባለን። እንደ ቡድን ተጫዋቾቻችን ለፍተዋል የሚችሉትን አድርገዋል ፤ አንዳንድ ጊዜ እግርኳስ ጎሎችን ማግባት እስካልቻልክ ድረስ ዋጋ መክፈልህ አይቀርም ተጋጣሚያችን በሁለት አጋጣሚዎች ወደፊት ሄዶ አንድ አገባ እኛ ግን የደረስነውን ያህል ማስቆጠር ስላልቻልን ነጥቡን ጥለን ወጣን።”