በምሽቱ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታቸውን ያለ ግብ ፈፅመዋል።
ከአቻ የተመለሱት ኢትዮጵያ መድኖች ከመጨረሻ ጨዋታቸው ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ዳግማዊ ዓባይ ፣ ዋንጫ ቱት ፣ አዲስ ተስፋዬ አስወጥተው በምትካቸው በረከት ከካሌብ ፣ ምንተስኖት አዳነ እና ጋቶች ፖኖምን ተክተው በማስገባት ሲጀምሩ በአንፃሩ በተመሳሳይ በመጨረሻ ጨዋታቸው አቻ የተለያዩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ በመጨረሻ ጨዋታ የተጠቀሙበትን የመጀመሪያ 11 ሳይቀይሩ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ መድኖች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መድኖች እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የነበራቸው አፈፃፀም ግን እጅግ ደካማ ነበር።
በአንፃሩ ኤሌክትሪኮች በብዙ መመዘኛዎች ሁለተኛ በነበሩበት አጋማሽ በነበራቸው ያነሰ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ተጋጣሚያቸው ላይ የመልሶ ማጥቃት ስጋት መደቀን ተስኗቸው ተስተውሏል።
ተመሳሳይ ይዘት በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአንፃራዊነት የተሻለ የመልሶ ማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ቢመስልም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር አንሰው በተደጋጋሚ በመገኘታቸው ጥቃታቸው ፍሬ ማፍራት ሳይችል ቀርቷል።
በብዙ መመዘኛዎች አሰልቺ የነበረው መርሃግብር ያለግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለቱ ቡድኖች የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ነጥባቸውን ማሳካት ችለዋል።