ጊኒዎች ቡድናቸውን ይፋ አድርገዋል

የዋልያዎቹ ቀጣይ ተጋጣሚ ስብስባቸውን ይፋ አድርገዋል።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የምትገጥመው እና በሚሼል ዱሱዬር የምትመራው ጊኒ በመጪዎቹ ሁለት የማጣርያ ጨዋታዎች የምትጠቀምበትን ስብስቧን ይፋ አድርጋለች።

የቦርስያ ዶትርሙንዱ አጥቂ ጒሬስይን ኢላክስ ሞሪባ እና ሌሎች ክዋክብቶችን በስብስባቸው ያካተቱት ጊኒዎች የማጣርያውን ሦስተኛ ጨዋታቸውን ለማድረግ ባስመዘገቡት ያሞሱክሩ በሚገኘው ስታድ ኮናን ባኒ ስቴድየም የሚያከናውኑ ሲሆን ኢትዮጵያም አቢጃን የሚገኘው ስታድ ደ ኢቢምፔ ስቴድየም ማስመዝገቧ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስብስብም ከፕሪምየር ሊጉ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ ሐሙስ ወይም አርብ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ፤ ከጊኒ ጋር በዘጠኝ አጋጣሚዎች የተገናኙት ዋልያዎቹ በስድስት ጨዋታዎች ሲሸነፉ በአንድ ጨዋታ አቻ ወጥተው እሁድ ጥቅምት ሦስት 1995 በአዲስ አበባ ስቴድየም በተካሄደ ጨዋታ ደግሞ በያሬድ አበጀ ብቸኛ ግብ  አንድ ለባዶ አሸንፈዋል።