ሪፖርት|  ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል

ፋሲል ከነማ እና ስሑል ሽረ በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል።

ዐፄዎቹ ከመጨረሻው ጨዋታ ቋሚ አሰላለፍ ብሩክ አማኑኤል፣ ኤፍሬም ኃይሉ፣ ቃልኪዳን ዘላለምን በእዮብ ማትያስ፣ አሚር ሙደሲር እና በረከት ግዛው ተክተው ሲገቡ ስሑል ሽረዎች ከሀዋሳ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ጨዋታው ገብተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ በወሰዱበት እና ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ነበር ፤
በአጋማሹ የመጀመርያ እና የመጨረሻ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት የተሻለ መንቀሳቀስ እየቻሉት ፋሲሎች በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ይበልጥ ወደ ሳጥኑ የተጠጋ የተደራጀ የኋላ ክፍል የነበራቸው ስሑል ሽረዎች በአንፃሩ በሁለት አጋጣሚዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ፋሲል አስማማው በግብ ጠባቂው ስህተት ያገኛት ኳስ መቶ በሀቢብ ከማል ጥረት በተመለሰችው ኳስ እና በአሰጋኘኝ ጴጥሮስ የቆመ ኳስ ሙከራ አማካኝነት ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።

በቁጥር ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የጎል ሙከራዎች በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥቂት የማይባሉ የጎል ዕድሎች ፈጥረዋል። ጃዕፈር ሙደሲር በፋሲል ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት ያገኛትን ኳስ ለዓብዱለጢፍ መሐመድ አቀብሎት ጋናዊው ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ሞክሯት ኦማስ ኦባሶጊ እንደምንም ባዳናት ኳስ ሙከራቸው የጀመሩት ሽረዎች በተመሳሳይ በፋሲል ተጫዋቾች የተግባቦት ክፍተት ያገኟት ዕድልም ትጠቀሳለች።

በመጀመርያው አጋማሽ የተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት ሰብረው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ተቸግረው የነበሩት ፋሲሎችም በሁለተኛው አጋማሽ በቃልኪዳን ዘላለም፣ አፍቅሮት ሰለሞን እና ማርቲን ኪዛ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ማርቲን ኪዛ ከመዓዘን የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ እና አፍቅሮት በተጋጣሚ ሳጥን አግኝቶ ያደረጋት ሙከራ የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።


ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ሁለተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤታቸው በማስመዝገብ ነጥባቸውን አምስት አድርሰዋል።