ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

በምሽቱ መርሃግብር ባህር ዳር ከተማ በፍጹም ዓለሙ እና መሳይ አገኘሁ ጎሎች ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ0 ረቷል።


ባህር ዳር ከተማዎች በሁለተኛው ሳምንት በአዳማ ከተማ 1-0 ከተሸነፉበት ስብስብ ፍጹም ፍትሕዓለው እና ወንድወሰን በለጠን አስወጥተው ወንድሜነህ ደረጄ እና ፍቅረሚካኤል ዓለሙን ሲያስገቡ በሁለተኛው ሳምንት አራፊ የነበሩት ሀዲያዎች በአንጻሩ በመጀመሪያ ሳምንት መቐለ 70 እንደርታን ከረቱበት ስብስብ በሰመረ ሀፍተይ እና በሁለት ቢጫ በወጣው አስጨናቂ ጸጋዬ ምትክ በየነ ባንጃ እና ብሩክ በየነን አስገብተዋል።

ምሽት 1 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የጣና ሞገዶቹ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫ መውሰድ ሲችሉ 15ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ፍጹም ዓለሙ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ ሲመልሰው ያንኑ ኳስ ያገኘው ሙጅብ ቃሲም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ነብሮቹ በኳስ ቁጥጥሩ እየተሻሻሉ ቢሄዱም አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ሲቀሩ ይባስ ብሎም በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ግን ግቦች ሊቆጠሩባቸው ነበር። ሆኖም ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ 42ኛው ደቂቃ ላይ ከፍጹም ዓለሙ 45+1ኛው ደቂቃ ላይ ከሙጅብ ቃሲም የተደረጉበትን ሙከራዎች በጥሩ ሁኔታ ማገድ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች 57ኛው እና 60ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን አግኝተው ብሩክ በየነ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምባቸው ሲቀር የግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ብቃትም የሚደነቅ ነበር።


ከሁለቱ አደገኛ ሙከራዎች የተረፉት የጣና ሞገዶቹ 63ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሙጅብ ቃሲም ወደ ውስጥ ሲያሻግር ኳሱን ያገኘው ፍጹም ዓለሙ ወደ ግብነት ለውጦታል። ከግቡ በኋላም በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት ባህር ዳሮች 87ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የኳስ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም መሳይ አገኛሁ አስቆጥሮት 2ለ0 መርታት ችለዋል።