የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-0 ሀዲያ ሆሳዕና

”በአሳማኝ ሁኔታ ጨዋታውን አሸንፈናል ብዬ አስባለሁ።” አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው

”ተጋጣሚያችን በጣም ተረጋግቶ ኳስ ይዞ ነው የሚጫወተው እና ያንን መቆጣጠር አልቻልንም።” አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ

ባህር ዳር ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ0 በመርታት ወደ ድል ከተመለሰበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተከታዩን ብለዋል።

አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው…

”ጨዋታው እንዳየኸው በጣም ጠንካራ ነበር። ሀዲያ ጠንካራ ስብስብ ነው ያለው የነበረው ቡድኑ ሳይበተን ያሉትን ይዞ ባሉት ላይ ደግሞ የተሻለ ክለቡን ሚያጠናክሩ ተጫዋቾችን ቀላቅሎ ነው የመጣው እና እንዳየኸው በሜዳ ላይ ፈታኝ ነበር። አግሬሲቭ ይጫወታሉ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ይሞክራሉ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች አሏቸው ጉልበተኞች ናቸው አንድ ለአንድ ግንኙነት ላይም እንግዲህ ተጫዋቾቻችን ይሄንን ጫና ተቋቁመው እንደምታስታወሱት ከመሸነፍ ነው የመጣነው ያንን ወደ ማሸነፍ ለመመለስ የነበረን ጥረት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው ይሄ ደግሞ የክለባችን መለያ ነው ከአንድ ሽንፈት ቶሎ ወደ ማገገም የምንመጣበት መንገድ በጣም ደስ የሚል ነው እና ምናልባት ወደ እራሴ ካላደላሁ በአሳማኝ ሁኔታ ጨዋታውን አሸንፈናል ብዬ አስባለሁ”

በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ መዘናጋቶች ነበሩ እና ምክንያቱ ምን ነበር?

”አዎ ይጠበቃል ባዶ ለባዶ ነው የወጣነው ልክ ስትገባ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጫናዎች ይኖራሉ ሚጠበቅ ነው። ተጫዋቾቻችን ጨዋታውን ተቆጣጠረውታል። የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረናል መጠቀም አልቻልንም በዛ ስሜት ውስጥ ሆነው ነው የገቡት ነገር ግን የራሳችንን የጨዋታ መንገድ ተከትለን እስከመጨረሻው ድረስ ከሄድን ጎል እንደምናገኝ እናውቅ ነበር እና ከተጫዋቾችም ጋር ያደረግነው የእረፍት ሰዓት ውይይትም ያው ነው ስለዚህ ልክ እንደገባን እንዳልከው ትንሽ መዘናጋቶች ነበሩ በራሳችን ኳሶች የተፈጠሩ ሆኖም ግን ቶሎ ወደ ሪትሙ ለመመለስ ችለናል እና የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገናል።”

ከዚህ በፊት የቡድን ግንባታህ የመስመር አጥቂዎች ላይ ነበር አሁን አሁን ግን በተለይም ዛሬ በብዛት በመሃል ለመሃል የመሄድ ነገሮች አሉ እና ይሄን የጨዋታ መንገድ ትቀጥላላችሁ?

“እንመጣበታለን። ሁሌም ሞር እኩል አድርገን መጫወት ነው የመጀመሪያ ምርጫችን እንግዲህ የተለያዩ ተጫዋቾችን ለማየት ሞክረናል። በምንከተለው የጨዋታው መንገድ የዛሬ ጨዋታ ደግሞ ከክለቡ ከተጋጣሚያችን ከሚከተለው ጨዋታ ጋር ተያይዞ የመሃል ሜዳ ብልጫውን ለመቆጣጠር ለመውሰድ ይሄኛውን የጨዋታ መንገድ ተጠቅመን ነው የገባነው። ለዚህኛው ጨዋታ መንገድ የሚሆኑ ተጫዋቾችን በሜዳው ላይ ለመጠቀም ሞክረናል። እንደአጠቃላይ ግን በመስመር የመጫወት እንቅስቃሴው ለቲማችን ትልቁ የማጥቂያ መንገድ ነው እና የበለጠ አጠናክረነው የምንቀጥል ነው የሚሆነው።”

አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ – ሀዲያ ሆሳዕና

ጨዋታው እንዴት ነበር?

“ከመጀመሪያው ጀምሮ ትክክል አልነበረም ጥሩ አልነበርንም። በመጀመሪያው ግማሽም የነበሩ ክፍተቶች በጣም ሰፊ ነበሩ ተረጋግተን አልበረም ስንጫወት የነበረው በተቃራነው ደግሞ ተጋጣሚያችን በጣም ተረጋግቶ ኳስ ይዞ አደራጅቶ ነበር የሚጫወተው ያን መቆጣጠር አልቻልንም። ይሄ ችኮላ አለ በጣም ችኮላ አለ አለመረጋጋቶች የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በጣም በሰፊው ነበር እነዛን ለማስተካከል ሞክረናል በተወሰነ መልኩ ሰከንድ ሀፍ ላይ ግን ጥሩ አይደለንም በዛው አንደኛ አጋማሽ ላይ እንዳለ ነው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የነበረው እና ያው ግብ ማግባቱ ወይንም ደግሞ ብዙ የጎል አጋጣሚዎችን እድሎችን ሰጥተናል ለተጋጣሚያችን ብቻ የተሻለ ነበር ተጋጣሚያችን በሁለቱም አጋማሾች በጣም የተሻለ ነበር።”

ብሩክ በየነ ግብ መሆን ሚችሉ ሁለት አጋጣሚዎችን በራሱ ጥረት አግኝቶ ሳይጠቀም መቅረቱ አሁንም ጫና ውስጥ እንዳለ ምልክት ይሆናል?

“ያው በሥራ ነው ብሩክ ምናልባት በፊት ኢትዮጵያ ቡና በነበረበት ሰዓት እንደዚህ አይነት ጫናዎች ነበሩ እኛ ጋር ግን እንደዛ አይነት ጫና የለም በቀጣይ ያስተካክላል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ለምን አቅም ያለው ልጅ ነው ጎል የማግባት አቅሙን አሁን ማሳደግ አለበት ስነልቦናውን ማሳደግ አለበት ያሳድጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ አጋጣሚዎችን በደንብ መጠቀም እንዲችል። ዛሬ በእርግጥ በራሱ ጥረት ያገኛቸውን ኳሶች ሚስ አድርጓል ቀጣይ ያስተካክላል የሚል እምነት አለኝ’።’

አሸንፋችሁ በሁለተኛው ሳምንት አራፊ ነበራችሁ እና እረፍቱ ተፅዕኖ አለው?

“እረፍቱ ለእኛ እንዲያውም ጥሩ አጋጣሚ ነው በቂ ሥራ እንድንሠራ ትንሽ ጉዳት ላይም የነበሩ ልጆች እንዲያገግሙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ብለን ነው ምናስበው እኛ እንደቡድን ፤ ግን ዛሬ አቀራረባችን ሙሉ ለሙሉ ተጋጣሚያችን ተቆጣጥሯል ማለት እችላለሁ ለምን የኳሱን ፍሰት ሙሉ ተቆጣጥረው ነው የሚጫወቱት እኛ ደግሞ በተቃራኒ ተረጋግተን መጫወት አልቻልንም። የጎል አጋጣሚዎችን የመፍጠር አቅማችን በጣም አነስተኛ ነበር። እንደከዚህ በፊት እንደነበረው እንቅስቃሴያችን አይደለም አልተጠቀምንም እረፍታችንን ጥሩ ነው ለኛ ለዝግጅትም ለተጎዱ ተጫዋቾችም በጣም የተሻለ ጊዜ ነው ያሳለፍነው።”