ጋናዊው ተከላካይ ወደ ወልዋሎ ለማምራት ከጫፍ ደርሷል

ኢያሱ ለገሰን ለረዥም ጊዜያት እንደሚያጡ ያረጋገጡት ቢጫዎቹ ተጫዋቹን ለመተካት ወደ ገበያ ወጥተዋል።

ኢያሱ ለገሰን ለረዥም ጊዜ በጉዳት እንደሚያጡት ካረጋገጡ በኋላ ተጫዋቹን ለመተካት በእንቅስቃሴ ላይ የቆዩት ወልዋሎዎች ጋናዊ ተከላካይ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል። ቡድኑን ለመቀላቀል ከስምምነት የደረሰው ተጫዋች ደግሞ የመሃል ተከላካዩ ሰሎሞን አዶማኮ ነው። የሃያ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው እና በያንግ አፖስትልስ፣ አክራ ግሬት ኦሎምፒክ እና ለእስራኤሉ ክለብ ሃፖኤል ኢሮኒ ሪሾን ሌዝዮን መጫወት የቻለው ይህ ተከላካይ ባለፈው የውድድር ዓመት በአልጀሪያ በተዘጋጀው የቻን አፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻለ ሲሆን ቀደም ብሎ ወልዋሎን ከተቀላቀለው ራዛቅ ቃሲም ቀጥሎ በዚህ የዝውውር መስኮት ከግሬት ኦሎምፒክ ክለቡን የተቀላቀለ ሁለተኛ ጋናዊ ሆኗል። ተጫዋቹ በቀጣይ ቀናት ኢትዮጵያ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የሕክምና ምርመራውን ካገባደደ በኋላም በይፋ ክለቡን የሚቀላቀል ይሆናል።

ቀደም ብሎ በቻን አፍሪካ ዋንጫ ጋናን ያገለገሉት ኢብራሂም ዳንላድ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ሸሪፍ መሐመድ ወደ መቐለ 70 እንደርታ፣ ራዛቅ ቃሲም ደግሞ ወደ ወልዋሎ ማምራታቸው የሚታወስ ነው፤ ሰሎሞን አዶማኮ ወደ ቢጫዎቹ የሚያደርገው ዝውውር የሚያገባድድ ከሆነው የስብስቡ አካል የነበረ እና በዝውውር መስኮት ወደ ኢትዮጵያ ክለብ የፈረመ አራተኛ ተጫዋች ይሆናል።

ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት ወልዋሎዎች በነገው ዕለት መስከረም 23 ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።