ሪፖርት | ቡናማዎቹ ሀዋሳ ከተማን ረተዋል

በሊጉ ለ53 ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በቡናማዎቹ 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ቡናማዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከገጠመው ቡድናቸው ጉዳት ባስተናገደው ስንታየሁ ዋለጪ ቦታ ይታገሱ ታሪኩን ሲተኩ ከስሑል ሽረ ጋር በመጨረሻ ደቂቃ ጎል አቻ በተለያዩት ሀዋሳ ከተማዎች በኩል በተደረገ የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ ሠለሞን ወዴሳ ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና ተባረክ ሄፋሞ ወጥተው ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ግርማ በቀለ እና ቢኒያም በላይ በቋሚ አሰላለፍ ተካተዋል።

10 ሰዓት ሲል የሊጉን 53ኛ ግንኙነታቸውን ያደረጉትን ሁለቱን ቡድኖች በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክርን የተመለከትንበት ነበር ፤ ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያውን ሰጥተው መጫወትን የመረጡት ቡናማዎቹ በራምኬል ጀምስ የ2ኛ ደቂቃ የግንባር ሙከራን ካደረጉ ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ሀዋሳዎች ግልፅ የማግባት ዕድልን ፈጥረው ተስተውሏል ፣ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው ከቀኝ መስመር ዓሊ ካልተጠቀመባት ሙከራ በኋላ እስራኤል እሸቱ አግኝቷት አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ውጪ ሰዷታል።

መሐል ላይ በቁጥር በዝተው በንክኪ ወደ ግራ መስመር አንተነህን የሚፈልጉ ኳሶችን መጠቀምን ያዘወተሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከዚሁ የማጥቂያ ቦታ ሁለት አጋጣሚዎች በአንተነህ መፍጠር ችለዊል። በይበልጥ ግለቱ ከፍ እያለ በመዲናይቱ ቡድን የበላይነት እየተጓዘ የነበረው ጨዋታ 24ኛው ደቂቃ ጎልን አስመልክቶናል።

በጥሩ ሂደት የሀዋሳ የግብ ክልል የደረሱት ቡናማዎቹ ይታገሱ ታሪኩ ወደ ውስጥ ያሳለፊትን ኳስ ወንድማገኝ ማዕረግ ለግብ ጠባቂው ሰይድ በግንባር ለመስጠት ሲሞክር ከኋላው የነበረው ኮንኮኒ ሀፊዝ ደርሳው ጎል አድርጓታል።

ከግቧ የተነቃቁት ቡናማዎቹ በደቂቃዎች ልዩነት ሁለተኛ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ፤ በፍቃዱ አለማየሁ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ የግቡ አግዳሚ ብረትን ለትማ ኳሷ ወጥታለች።

በተጋጣሚያቸው በብዙ ረገድ ለመበለጥ የተገደዱት ሀዋሳዎች ብልጫ በተወሰደባቸውን የመሐል ክፍል 36ኛው ደቂቃ ግርማ በቀለን በማስወጣት አቤኔዘር ዮሐንስ ተክተው ማስተካከልን ቢያልሙም አጋማሹ በ1ለ0 ውጤት ተጋምሷል።

ከዕረፍት ሲመለሱ መሻሻሎችን ይዘው የገቡት ሀዋሳ ከተማዎች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች አቻ ለመሆን ያደረጉት ጥረት በ47ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ቢኒያም በላይ ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻማ እስራኤል በግንባር ገጭቶ ያመቻቸለትን ኳስ ዓሊ ሱለይማን በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሯታል።

በብዙ መልኩ ተዳክሞ የቀጠለው ጨዋታው በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ቀስ በቀስ ዳግም ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከቆሙ ኳሶች እና ወደ ቀኝ የአማኑኤል አድማሱን ፈጣን ሽግግር መጠቀምን ያደረጓቸው ጥቃቶች በ76ኛው ደቂቃ በፍቃዱ አለማየሁ ከማዕዘን ሲያሻማ ራምኬል ጀምስ በግንባር ገጭቶ የሰይድ መረብ ላይ አሳርፏታል።



የኢትዮጵያ ቡናን ፈጣን የማጥቂያ መንገድን መቋቋም እየተሳናቸው የመጡት ሀይቆቹ 79ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል በጥልቀት ወደ ውስጥ ከቀኝ ያሻገረውን ኳስ የሀዋሳ ተከላካዮች ስህተት ታክሎበት ዳዊት ሽፈራው ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በቡናማዎቹ 3ለ1 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።