የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 3-1 ሀዋሳ ከተማ

”እኛ እንደ አዲስ አይደለም ራሳችንን ምንቆጥረው” አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ

”ቦነስ ነው ዛሬ የሰጠናቸው” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማን 3ለ1 ከረታበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው..

“ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ከባለፈው ጨዋታ ቢያንስ ያገኘነውን ዕድል ወደ ጎልነት በመቀየር የተሻለ ነበር። ግን አሁንም ይቀረናል መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ማሸነፍ ውስጥም ይሄን ነገር ማስተካከል ደግሞ የበለጠ ጥሩ ነው እና እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ በጨዋታው።”

በመጀመሪያ አጋማሽ ከነበረው እንቅስቃሴ ሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ አካባቢ መቀዛቀዝ ነበር ከምን የመጣ ነው?

“አዎ ተዘናግተናል መጀመሪያ ላይ ብዙ ዕድሎች ነበሩ። ሶስት አራት ጎሎችን ማግባት የነበረብን ነበር ከእረፍት በፊት ከእረፍት በኋላ ግን ገና ወደ ጨዋታ ለመግባት የእነሱን ጠንካራ ነገር ማቆም አለብን። ፈጣን አጥቂዎች አሏቸው እና ወደ ግብ ክልል እንዳይመጡብን ለመዝጋት ነበር ያሰብነው ነገር ግን መጨረሻ ፈቀድንላቸው። ቶሎ ግን ከዛ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጊዜ አልፈጀብንም። ስለዚህ የሚስተካከል ነገር አለ እርግጥ ነው ሁሉንም ጨዋታ ዘጠናውንም ደቂቃ በትኩረት መጫወት አለብን። ነገር ግን ከዛ በኋላ ወደ ጨዋታው የተመለስንበት ነገር ደግሞ የተጫዋቾቼን ጥንካሬ ያሳያል።”

እንደ አዲስ ስለሠሩት ቡድን እና ስለ ሦስት ነጥቡ ዋጋ?

”ትልቅ ዋጋ አለው። እኛ እንደ አዲስ አይደለም ራሳችንን የምንቆጥረው ማድረግ እንደሚችሉ ያምናሉ ተጫዋቾቹ  አቅም እንዳላቸው ሁሌም እናወራለን ፤ ስለዚህ የበለጠ ኮንፊደንስ ይጨምርልናል። ከዝግጅት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ወደ ዘጠኝ ጨዋታ አስር ጨዋታ ነው የተጫወትነው አንድ ነው ሽንፈት የገጠመን። ስለዚህ አቅም አላቸው እነዚህ ተጫዋቾች እሱ ላይ የበለጠ እንሠራለን።”

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

“ጨዋታው በእንቅስቃሴ ደረጃ መጥፎ አይደለም። ምክንያቱም ሁለተኛው ኳስ እየተነጋገርን የቆመ ኳስ በአንድ ተጫዋች እንደሚጠቀሙ እየተነጋገርን ማርክ ያስደረግነው ተጨዋች ባለመያዙ ተጠቀመ። ከዛ በኋላ ተነሱ እንጂ በጣም ብልጫውን ወስደን ነበር። ጎሎች ጋር ብዙ ደርሰናል። የጎል አጋጣሚ ፈጥረናል። ቦነስ ነው ዛሬ የሰጠነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም እነሱ ጠብቀውን ነበር የእኛን ኳስ ሲጫወቱ የነበሩት። የምናበላሸውን ኳስ ነው የሚመጡት። በተለይ ሁለተኛ ኳስ መግባቱ እጅግ ዋጋ አስከፍሎናል። በተለይ የቀየርናቸው ተጫዋቾች እንደበፊቱ እንደምንፈልገው ባለማድረጋቸው ትንሽ የምንፈልገውን ነጥብ እንዳንይዝ አድርገውናል።”

በሁለተኛው አጋማሽ በፍጥነት ወደ ጨዋታው ተመልሳችሁ መቀጠል ስላለመቻላችሁ እና በመከላከል ላይ ያለውን ድክመት እንዴት ይገልፃሉ?

“በፍፁም እኔ ሁለተኛውን ኳስ አይተኸህ እንደሆነ ኮርና ኳስ ነው የገባው። ስለዚህ ማግባት አይደለም ብልጫውን በደንብ ሁለተኛው ጎል እስኪገባብን ድረስ በደንብ ኳስን ተቆጣጥረን ነበር ስንጫወት የነበረው። በፉልባኮቻችን እንሄዳለን፣ በስሩ ፓሶችም እናገኛለን፣ የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፣ ቶሎ ጎል ጋር እንደርስ ነበር። ነገር ግን ሁለተኛው ኳስ እንዳለ የእኛን እንቅስቃሴ ነው ያፈረሰው። ምክንያቱም የተነጋገርንበት መንገድ ስለነበር ያ አንድ ልጅ ባለመደረጉ ትንሽ ቲማችን ነጥብ አጥቷል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ቲማችን አሁንም በጣም ጠንካራ ቲም እንዳለን ነው ምንም ጥያቄ የለውም። ግን ወደአሸናፊነት ቶሎ መመለስ ያስፈልጋል። እንደዚህ ጥቃቅን የሚመስሉ ቲሙን ዋጋ የሚያስከፍሉ ነገሮችን ማረም ነው የሚያስፈልገው እንጂ ቲማችን ሙሉ ብልጫ ነበረው ማለት ይቻላል በደንብ ኳስን ተቆጣጥሮ ተጫውቷል”።