ሪፖርት | መቻሎች በጭማሪ ደቂቃ በተገኙ ግቦች ወላይታ ድቻን አሸንፈዋል

በምሽቱ መርሃግብር መቻሎች በጭማሪ ደቂቃ በተገኙ ሁለት ግቦች ታግዘው ወላይታ ድቻን በመርታት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

መቻሎች በመጨረሻ ጨዋታቸው በሲዳማ ቡና ከተረታው ስብስብ ለውጥ ሳያደርጉ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በአንፃሩ በድሬዳዋ ከተማ አሰቃቂ ሽንፈት ያስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ሙሉቀን አዲሱ እና ብስራት በቀለን አስወጥተው በምትካቸው ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ፀጋዬ ብርሃኑን በመጠቀም ጀምረዋል።

በብዙ መልኩ እጅግ ቀዝቃዛ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መቻሎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው የተጫወቱበት በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ አጋማሹን በጥንቃቄ ለመከወን የሞከሩበት ነበር።

ጥራታቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ብርቅ በነበሩበት ጨዋታ መቻሎች በ34ኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ የመቻሉ አምበል ምንይሉ ወንድሙ ከቆመ ኳስ መነሻ ያረገችውን አጋጣሚ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

መመራት የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በአንፃራዊነት አውንታዊ ሆነው በጨረሱት አጋማሽ በመቻሎች የ1ለ0 መሪነት የተጠናቀቀ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ የጨዋታውን ሂደት በመቻል አጋማሽ እንዲደረግ ማስገደድ ቢችሉም በ61ኛው ደቂቃ አብነት ደምሴ ከሳጥን ጠርዝ ከተገኘ የቅጣት ምት በቀጥታ የሞከራት እና አልዊንዞ ናፊያን በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።

የድቻዎች ጥረት ፍሬ አፍርቶ በ72ኛው ደቂቃ የሚገባቸውን የአቻነት ግብ አግኝተዋል ፤ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ የመታት ኳስ የመቻልን የግብ ዘብ አልፋ ቡድኗን አቻ አድርጋለች።


በቀሪዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች የአሸናፊነቷን ግብ ፍለጋ በተሻለ መልኩ ጥረት ቢያደርጉም መቻሎች ግን ሳይጠበቁ ሁለት ግቦችን በጭማሪ ደቂቃ መግኘት ችለዋል ፤ 91ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ በረከት ደስታ ያደረሰውን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ እንዲሁም ራሱ በረከት ደስታ ደግሞ በ93ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በመቻሎች ድል አድራጊነት ተጠናቋል