”ስታሸንፍ ሁሌም ጨዋታው ጥሩ ነው ፤ መጥፎም ብትሆን” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ
”እየተሸነፍን ያለነው ቀላል በሆኑ የመከላከል ስህተቶች ነው።” አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ
መቻሎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ግቦች ወላይታ ድቻን 3ለ1 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ካሳኩበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ነበራቸው።
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል
ጨዋታው እንዴት ነበር?
”ጥሩ ነው። ስታሸንፍ ሁሌም ጥሩ እኮ ነው መጥፎም ብትሆንም ፤ ግን በአጠቃላይ ጥሩ ነው የጨዋታው እንቅስቃሴያችን እኛ በያዝነው መንገድ ነው የተጫወትነው ፤ ያን ነገር አንለቅም እስከመጨረሻው ምክንያቱም በዕቅዳችን በዝግጅታችን የሠራነውን ነገር ጨዋታ ወይ በተሸነፍን ቁጥር ወይም ተፎካካሪ በጠነከረ ቁጥር ባለ ቁጥር ያን ጨዋታ መለወጥ አንፈልግም እና ጥሩ ነው እንቅስቃሴያችን በተከታታይ ያደረግነው።”
በመጀመሪያ አጋማሽ የነበረውን ጥንካሬያችሁን በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች የማጣታችሁ ምክንያት ምንድን ነው?
”ተጫዋቾት ወደ ኋላ ስላፈገፈጉ ነው ፤ ሌላ እኮ የሚታይ ነው። ምክንያቱም ወደ ውጪ መውጣት አልፈለጉም፤ እኛ ይህንን አላልናቸውም። ግን ግቡ ከገባ በኋላ እንደገና መውጣት ጀመሩ ይሄ በእነሱ ነው። ስለዚህ ያ ነው ስህተቱ እና ያ ደግሞ የሚታረም ነው ፤ ከጉጉት ነው። ምክንያቱም ባለፈው ተሸንፈው ስለነበር የያዙትን ነገር ይዘው መውጣት ስለሚፈልጉ ነው።”
በአማኑኤል እና ነስረዲን ጉዳት አስገዳጅ ቅያሪ አድርገው ዳዊት ማሞን ባልተለመደ ቦታ ስላጫወቱት የጨዋታው እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ነበር?
”አልፈጠረም። ዳዊት ሁሉም ቦታ መጫወት የሚችል ነው። ዳዊት ሁለገብ ነው። የመሃል ተከላካይ መሆን ይችላል። ምናልባት ግብ ጠባቂ ካልሞከርነው እንጂ ሁሉንም መሆን ይችላል እና ብዙ ችግር የለውም። ያው ብሔራዊ ወጣት ቡድን ላይ ሁለት ልጆች ሄደውብናል። በኃይሉ በቤተሰብ ችግር ምክያንት የለም። እነዚህ ተጫዋቾች ሲመጡ ቡድናችን ይበልጥ ጥሩ ሆኖ ይሟላል ብዬ አስባለሁ።”
በዕረፍት ሰዓት ቡድኑን ለማጠናከር ተጨማሪ ዝውውሮች ይኖሩ ይሆን?
”ካለን እናደርጋለን። የሦስት እና አራት ተጫዋች ቦታ አለን። ለኛ የሚሆን ተጫዋች ካገኘን እና ከቡድናችን ጋር የሚመጥን ከሆነ እናደርጋለን።”
አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ
ስለ ጨዋታው..
”ጨዋታው ጥሩ ነበር። እንግዲህ ያው ሦስት ለአንድ ተጠናቋል ባለቀ ሰዓት በተቆጠሩብን ሁለት ጎሎች ውጤት ጥለን ወጥተናል።”
ከዕረፍት በኋላ ተጭናችሁ ወደ ጨዋታው ተመልሳችሁ አቻ መሆን ችላችሁ ነበር እና ከዛ በኋላ ምንድን ነው የተፈጠረው?
”ሁለት ለአንድ ስንሆን ሁለት እኩል ለማድረግ ተጫዋቾች እንዳለ አጥቅተው ለመጫወት ሰዓቱም አልቆ ስለነበር ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር እና አቻ ለማድረግ ያችን የተሳሳቷትን ነገር ለማረም በሄድንበት በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ተጠቀሙ እና ሦስተኛ ጎል ሊገባብን ቻለ እንጂ በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር ሲጫወቱ የነበሩት ተጫዋቾቹ።”
ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት አስተናግዳችኋል እና ከዚህ ለመውጣት ምን ታስባለህ?
”መሥራት ነው። ሌላ ምንም መፍትሔ የለውም። ሠርተን እንግዲህ ለመውጣት ነው ጥረት የምናደርገው። ያጋጥማል እግር ኳስ ላይ ከችግሮቹ ለመውጣት የግድ መሥራት ይጠበቅብናል ፣ ያንን አሻሽለን ለመቅረብ ነው የምንጥረው።”
በሁለቱ ጨዋታዎች የተቆጠሩ 7 ጎሎች በመከለከሉ ረገድ ክፍተት እንዳለ ያሳያሉ?
”ያሳያል። የጥንቃቄ ጉድለቶች አሉ። ከማትጠብቃቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አንፃር ኤክስፔክት የማታደርጋቸው ስህተቶችን ሲሠሩ ነው እየገቡብን ያሉት እና ሉዝ እያደረግን ያለንበት መንገድ በጣም ቀላል በሆነ የመከላከል ስህተቶች ነው። መሠረታዊ ነገር እየሰሩ በጣም ትናንሽ የሆኑትን በጣም ቀላል የሆኑትን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው በመዘናጋታቸው ስኮር እየተረገብን ነው።”