ሊጉ በአህጉራዊ ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት የሚደረጉ የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አርባምንጭ ከተማ
በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ቻምፒየኖቹ ንግድ ባንኮች የዓመቱን ዐይን ገላጭ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ከሚገቡት አዞዎቹ ጋር ከስምንት ዓመታት በኋላ የሚያደርጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በአህጉራዊ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ቻምፒዮኖቹ ንግድ ባንኮች በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረው የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታቸው በመራዘሙ እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ከውድድሩ መውጣቱን ተከትሎ በሁለቱም ሳምንታት ጨዋታ ያላከናወኑት ቻምፒየኖቹ ዓመቱን በድል ለመጀመር ከአዞዎቹ ጋር ይጫወታሉ። የሊጉን ዋንጫ ያሳካውን ጠንካራውን ስብስባቸው ይዘው የቀጠሉት አሰልጣኝ በጸሎት ከአህጉራዊ ውድድር በኋላ ለሁለት ሳምንታት ጨዋታ ያላከናወነውን ቡድናቸውን አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዝግጁነቱን ከፍ አድርጎ የማቅረብ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት አስተናግደው ዓመቱን የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ ከኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ ተለያይተው አንድ ነጥብ በማስመዝገብ ወደ ነገው ጨዋታ ያመራሉ። ነጥብ በተጋሩበት መርሐግብር ከመጀመርያው ጨዋታ አንፃር በብዙ መመዘኛዎች ተቀዛቅዘው የቀረቡት አርባምንጮች አህመድ ሁሴንን ዒላማ ያደረጉ ኳሶች ላይ የተንጠለጠለው የማጥቃት አቀራረባቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ቡድኑ ከተጋጣሚው አንፃር የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የነበረው ውጤታማነት ይበልጥ መሻሻልን ይፈልጋል። በነገው ዕለት ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት በጨዋታ በአማካይ 0.9 ግብ ብቻ ያስተናገደው እና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ከነበራቸው ክለቦች አንዱ የነበረውን ንግድ ባንክ እንደመግጠማቸው በብዙ መለኪያዎች የላቀ እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ነገ ከ2009 የውድድር ዘመን በኋላ የመጀመርያ ጊዜ በሊጉ ይገናኛሉ። በሊጉ በአጠቃላይ 12 ጊዜ ተገናኝተው ሦስት ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ ስድስቱን አቻ ተለያይተዋል። ባንክ 15 ግቦች፣ አርባምንጭ 14 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
በንግድ ባንኮች በኩል ባለፈው የውድድር ዓመት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት የአራት ጨዋታዎች ቅጣት የተላለፈበት ሳይመን ፒተርን አያሰልፉም ከዛ በተጨማሪም የፈቱዲን ጀማል መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። አዞዎቹ በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው አበበ ጥላሁንን በቅጣት ከኢትዮጵያ መድን በነበረው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ሳሙኤል አስፈሪን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።
ሲዳማ ቡና ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ
የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሐግብር ድሉን ለማስቀጠል ወደ የሜዳ የሚገባው ሲዳማ ቡና እና የመጀመርያ ነጥብ ፍለጋ ላይ ያለውን ወልዋሎን ያገናኛል።
ከመጀመሪያው የሀዋሳ ከተማ ሽንፈት በማገገም ጠንካራው መቻልን ሁለት ለአንድ ያሸነፉት ሲዳማ ቡናዎች ከመጀመርያው ጨዋታቸው አንፃር የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ድርሻ አመርቂ ባይሆንም የማጥቃት ጥንካሬያቸውን ማስቀጠል ችለዋል። በመጨረሻው ጨዋታ ጥቂት የማይባሉ ዒላማቸው የጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ የቻለው ጥምረቱ በነገው ዕለትም በተመሳሳይ የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ መሆኑ አይቀሪ ነው። ቡድኑ በርከት ያሉ የግብ ምንጮች መያዙ እና የተለያየ ‘ፕሮፋይል’ ያላቸው ጥራት ያላቸው የፊት መስመር ተጫዋቾችን መያዙም የጥንካሬው ሌላ ማሳያ ነው። ሆኖም በመጨረሻው ጨዋታ ተጋጣሚው በርከት ያሉ ሙከራዎች እንዲያደርግ በር ከፋች የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው ውስን ለውጦች እንደሚሻ በጨዋታው ታይቷል። በጨዋታው የጦሩን ጥቃት በማምከን ተጠምዶ የዋለው ግብ ጠባዊው መስፍን ሙዜ ጥረት ባይታከልበት ከአንድ ጎል በላይ የሚያስተናግዱበት ዕድልም ነበር።
በተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት እና በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ነጥባቸውን ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡት ወልዋሎዎች ነጥብ ያልሰበሰበ የሊጉ ሁለተኛ ክለብ ሆኖ ላለመቀጠል ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከዋነኛው የፈጠራ ችግራቸው በተጨማሪ ለግለሰባዊ ስህተቶች የተጋለጠ የመከላከል አደረጃጀት የነበራቸው ቢጫዎቹ በነገው ዕለት በጥራትም ሆነ በጥልቀት የተሻለ የፊት መስመር ጥምረት ካለው ቡድን እንደመግጠማቸው በኋላ ክፍል የታዩባቸውን ክፍተቶች አርመው መቅረብ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ ዳዋ ሆቴሳን ከጉዳት መልስ ማግኘቱ በፊት መስመር ላይ ለውጦች ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ውጤታማ ያላደረገውን የረዣዥም ኳሶች የማጥቃት አጨዋወትም ይቀይራል ተብሎ ይገመታል።
ሲዳማ ቡና አምስት ለባዶ ያሸነፈበት እና የተሰረዘውን የ2012 ጨዋታ ሳያካትት በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና ሁለቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ አምስት ሲያስቆጥር ወልዋሎ አንድ ማስቆጠር ችሏል።
ወልዋሎዎች ዳዋ ሆቴሳ ከጉዳት ሲመለስላቸው
ነጋሲ ገብረኢየሱስ፣ ሔኖክ ገብረእግዚአብሔር እና ስምዖን ማሩ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ናቸው። ከሃያ ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር ያለው ሰለሞን ገመቹም ሌላ በጨዋታው የማይሳተፍ ተጫዋች ነው። ሲዳማ ቡናዎች በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች ባይኖርም ደግፌ ዓለሙ እና መስፍን ሙዜ ከሃያ ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር በመሆናቸው የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል።