ወልዋሎዎች የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል

ደካማ አጀማመርን በሊጉ እያደረጉ የሚገኙት ቢጫዎቹ ሁለት አማካዮችን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በትናንትናው ዕለት ጋናዊው ተከላካይ አዶማኮ ሰሎሞንን ለማስፈረም ከስምምነት የደረሱት በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ወልዋሎዎች ሁለት አማካዮች አስፈርመዋል።
ወደ ቡድኑ የተቀላቀለው የመጀመሪያው አማካይ ዮናስ ገረመው ሆኗል ፤ ሀላባ ከተማን ለቆ በ2006 ወደ ኢትዮጵያ ቡና ካመራ በኋላ በቡናማዎቹ ቤት የሁለት ዓመት ቆይታን በማድረግ ከዚያም በድሬዳዋ ከተማ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በተከታታይ ባነሳባቸው ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ ፣ ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ከተጫወተ በኋላ ወደ ወልዋሎ አቅንቷል።

ሁለተኛው ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ሳምሶን ጥላሁን ነው ፤ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ባህርዳር ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ መጫወት የቻለው አማካዩ በይፋ ፊርማውን አኑሯል።