አሰልጣኝ ስዩም ከበደ መግለጫ ሰጥተዋል

👉 “ለብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ መቅረት እንደ ሀገር ክስረት ነው።”

👉 “እኔ ላልኖር እችላለሁ ውድድሩ ላይ ፤ ግን ተጫዋች የመምረጥ አቅሙ የለኝም ማለት አይደለም።”

👉 “እንደ አጠቃላይ እንደ ሀገር ያለው ነገር በገሃድ የምናውቀው እድሜ ማጭበርበር ነው። ይሄ ካልተቀረፈ እንደ ሀገር ማደግ አንችልም።”

👉 “ውጪ ናቸው ስለተባሉ ብቻ ግን ጥሩ ናቸው ማለት አይደለም እዚህ ከመርጥናቸው የማይሻሉም ነበሩ።”

የኢትዮጵያ ከ20 አመት ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ለሚያደርጋው የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዝግጅቱን እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገላቸውን መንገድ ከማስረዳት ተነስተው የእያንዳንዳቸውን የኮቺንግ ስታፉን ፕሮፋይል እና ከዚህ በፊት የሰሩበትን ስራ ይፋ ካደረጉ በኋላ ለተጫዋቾት ጥሪ ያደረጉበትን መንገድ አስረድተዋል።

“የተጫዋቾችን ምርጫ ስናደርግ ከ90% በላይ በእነዚህ ወጣት አሰልጣኞች ኢንቮልቭ እንዲያደርጉ ብዙ ኃላፊነት በመስጠት ነው ምርጫ ያደረግነው” ካሉ በኋላ “የቴክኒክ ክፍሉ በ U20 ውድድር ላይ ወይንም በፕሪሚየር ሊግ ላይ በቅርብ ጊዜ ያደጉ ተጫዋችች ሊስት አድርጎ ሰጥቶን ነበር ከእዛ ጨምቀን ተነጋግረን ነው ጥሪ ያደረግነው።” ብለዋል። ስለነበረው ጥሪ ሲያስረዱም  በመጀመሪያ ጥሪ ለ 41 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው 33 ተጫዋቾች ብቻ ተገኝተው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንዳልተገኙ አስረድተዋል።

የነበረው ጊዜ በጣም አጭር ከመሆኑ አንፃር ምዝገባው በጣም የተጣደፈ መሆኑን ያነሱት አሰልጣኙ ከመረጡት ሃያ ተጫዋቾች ውስጥ ለክለብ ጨዋታቸውን ለማድረግ አንዳንድ ተጫዋቾች በመሄዳቸው ምክንያት ምርጥ አስራ አንድ ቋሚ አሰላለፍ ለመምረጥ መቸገራቸውን ገልፀዋል። አክለውም ከጅቡት ጋር የነበራቸው ሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች ጠቃሚ እንደነበሩ ተናግረዋል። “በጨዋታዎቹም ሆነ በድግግሞሽ በተንቀሳቃሽ ምስል በማስደገፍ ምንፈልገውን ነገር እና የምንከተለውን የአጨዋወት ፍልስፍና ለተጫዋቾቹ ለማሳየት ጥረት አድርገናል ብለዋል።”

አሰልጣኙ አክለውም እርግጠኛ የሆነ የእድሜ አሰራር እኛ ሀገር የተለመደ አይደለም ያንን ማድረግ እንደ ሀገር ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ ክለቦች ኃላፊነት ወስደው በትክክል የእድሜ ጉዳይ ከታች ጀምሮ ከ17 አመት በታች ከ20 አመት እየተባለ ካላደገ በዚህ የሚሰራው አሰራር ትክክል ካልሆነ ከ17 አመት በታች ከሚለው ብቻ መመረጥ አለበት ከ20 በታች ከሆነ ደግሞ ከ20 ውድድር ብቻ መመረጥ አለበት። ሊግ ላይ ገብተው እየተጫወቱ እድሜያቸው የፈቀደላቸውም ብቅ ያሉ በትላልቅ ደረጃ ላይ ላሉም ጥሩ አድርገናል ብለዋል። በተጨማሪም እንደሀገር ካልተሰራ ስንጥር እያወጣን መቀጠላችን አይቀሬ ነው ብለዋል።

የምንሄድበት ውድድር ጠንካራ ነው ያሉት አሰልጣኙ ተጋጣሚዎቻችን በትክክለኛ እድሜ አይመጡም እና እኛው እዚህ አጭበርብረን እንሂድ ሳይሆን የምናደርገውን ለማድረግ ሞክረናል ብለዋል። አያይዘውም ከውጭ የመጡ ተጫዋቾች መዘገየታቸው ነው እንጂ ለእኔ በጣም ይጠቅሙኝ ነበር ጠንክረው ከሠሩ ለብሔራዊ ቡድንም መብቃት የሚችሉ ነበሩ። ሁሉም ግን አይደለም መጥተውም እኛ ከመረጥናቸው ልጆች የተሻለ ነገር የሌላቸውም ነበሩም ብለዋል።

ከጊዜው ጋር በተያያዘም ”ትልቁ ፈተና የሆነብን አንድ ጨዋታ ብቻ አድርገን የምንመጣበት ውድድር አለመሆኑ እና ቶርናመንት መሆኑ ነው ያሉት አሰልጣኙ ጨዋታ ቢያንስ ሶስት ነው ከምድብ ካለፍን ደግሞ አራት አምስት እያለ ይቀጥላል ስለዚህ ቢያንስ 23 ተጫዋች መያዝ ነበረብን ግን ያ እድል አልተፈጠረም። ከምዝገባው ህግ ጋር እና ከተለያዩ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ ሃያ እንኳን አልደረሱም አስራ ስምንት ብቻ ናቸው ካሉ በኋላ በጥቅሉ ለውድድሩ ጠንካራ ሆኖ ለመገኘት መሥራት ያለብንን ሥራ ሠርተናል በማለት ዛሬ ማታ ጉዟቸውን እንደሚጀምሩ አሳውቀዋል።

በመጨረሻም አሰልጣኙ ከጋዜጠኞቹ ለተሰነዘሩት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። ከጥያቄዎቹ መካከልም

ያልተመለከቷቸውን ተጫዋቾች ስለመምረጣቸው እና ከ20 ዓመት በታች ውድድድ ላይ ጥሩ ሆነው ሳይመረጡ ስለቀሩት ተጫዋቾች…

”እንደነገርኳችሁ እዚህ ምርጫ ላይ የእኔ ረዳቶች ውድድሩ ላይ የተመለከቷቸው እና የሚያውቋቸውን ይመጥናሉ ያሏቸውን ነው። እስከመጨረሻው መሄድ ያለብንን ነገር ሄደን ነው የመረጥናቸው። እኔ ላልኖር እችላለሁ ውድድሩ ላይ ግን ተጫዋች የመምረጥ አቅሙ የለኝም ማለት አይደለም።”

ከእድሜ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ?

”በሁሉም እድሜ እርከን የእድሜ ችግሮች አሉ። ከ17 ዓመት በታች ብትሄድም ከ20 ዓመት በታች እድሜያቸው ልክ አይደለም። ከእዛ የሚበልጡ ነው ያሉት በክለብ ደረጃ የምናውቀው ነው። እንደ አጠቃላይ እንደ ሀገር ያለው ነገር በገሃድ የምናውቀው እድሜ ማጭበርበር ነው። ይሄ ካልተቀረፈ እንደ ሀገር ማደግ አንችልም ብሔራዊ ቡድኑም ማደግ አይችልም። እንደ ሀገር ሲስተም እንዲዘረጋ ጉዳዩ የእናንተ የጋዜጠኞችም ጭምር ነው እና መሥራት አለብን።”

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጎላቸው ያልመጡበት ምክንያት ምንድነው? ስላልመጡስ ምንድነው የሚጠብቃቸው?

”ጥሪ ስናደርግ ለሁሉም ክለብ ተጫዋቾች ነው ያደረግነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ምክንያታቸውን አናውቅም። በግል የቡድን መሪዎች ጋር አውርቼ ያገኘሁት ምላሽ ተጫዋቾች ውጪ ሄደው ጠፍተዋል ውድድሩን በእነዚህ ልጆች ነው የምንመራው ነው ያሉኝ።”

በአጭር ጊዜ ቆይታቸው ስላሰቡት ነገር?

”የተሻሉ አሁን ብቅ ያሉ ልጆችን ይዘን ከ20 ዓመት በታች ጠንከር ያለ ቡድን ይዘን ለመቅረብ ነው የአጭር ጊዜ እቅዳችን። እንደ ቡድን ግንባታ ግን የተመቸ ነገር የለም። በዚህ ውድድር ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፈንን ከዞናችን የምናልፍበትን እቅድ ነው ከተጫዋቾቼም ጋር ያስቀመጥነው።”

ስድስት ተጫዋቾች ከውጪ መጥተው ስድስቱን ስላለመጠቀማቸው ተጠይቀው…

”መምጣታቸው አንድ ፖዘቲቭ ነገር ነበረው። ነገር ግን የኔ እጅ ባይኖረውም ፌዴሬሽኑ ለሚጫወቱበት አካባቢ ደብዳቤ ልኮ ነው የመጡት ነገር ግን የዝግጅት ጊዜያችንን ከጨረስን በኋላ ነው የመጡት። የውጪ ተጫዋቾች መጥተው ብቃታቸው ከፈቀደ የማይጫወቱበት ምክንያት የለም ፤ ቢሆንም ይመረጣል። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድንም ይፈጠራል። ውጪ ናቸው ስለተባሉ ብቻ ግን ጥሩ ናቸው ማለት አይደለም እዚህ ከመርጥናቸው የማይሻሉም ነበሩ።

ተጠርተው ስለማይገኙ ተጫዋቾች…

”ለብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ መቅረት እንደ ሀገር ክስረት ነው። ይሄንን ወደ ፊት ፌዴሬሽን ህግና ደንብ አውጥቶ ኮንትሮል የሚያደርግበትን ዘዴ መፍጠር አለበት እንጂ ነገም ሌሎች ክለቦች ላይልኩም ይችላሉ።”