ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓመቱን በድል ጀምሯል

ሁለት ጨዋታዎች ሳያደርግ በሦስተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3ለ1 በሆነ ውጤት አርባምንጭ ከተማን አሸንፏል።


ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በሁለት የተለያዩ ምክንያቶች ማድረግ ሳይችሉ የሦስተኛ የጨዋታ ሳምንታቸው ላይ የደረሱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ያገኟቸውን አብዱልከሪም መሐመድ እና ቢኒያም ካሳሁንን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካተው ሲገቡ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያለ ጎል ተለያይተው በነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በኩል ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ሳሙኤል አስፈሪ ፣ መሪሁን መስቀሌ እና አሸናፊ ተገኝ ወጥተው ስቴፈን ባዱ አኖርኬ ፣ ቻርለስ ሪባኑ እና በፍቅር ግዛቸው ተተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በፌድራል ዋና ዳኛ ባህሩ ተካ እየተመራ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ ፍፁማዊ ብልጫን ወስደው በፈጣን ሽግግሮች መጫወትን መርጠው የተንቀሳቀሱት ንግድ ባንኮች 2ኛው ደቂቃ ላይ ከዚህ የጨዋታ መንገድ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ባሲሩ ዑመር ይዞ የገባውን ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ውስጥ ሲያሻግር ኪቲካ ጅማ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎ ቡድኑ ቀዳሚ አድርጓል።

ፈጠን ካሉ ሽግግሮቻቸው በተጨማሪ የማጥቂያ በመስመሮች ጥቃት መስንዘር የቀጠሉት ንግድ ባንኮች በ7ኛው ደቂቃ የአርባምንጭ ተጫዋቾችን ጫና ውስጥ በመክተት ኳስን የነጠቀው ኪቲካ ጅማ እየነዳ ወደ ግብ ክልል ይዟት የሄዳትን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሮ ለቡድኑም ሆነ ለራሱ ሁለተኛ የሆነች ጎልን አክሏል።

አጀማመራቸው ጥሩ ያልነበረው እና ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት ተቸግረው የቆዩት አዞዎቹ ቀስ በቀስ በተሻጋሪ ኳሶች አህመድ ሁሴን በተሰለፈበት የግራ መስመር ማጥቃት የጀመሩ ሲሆን በ16ኛ ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል። አህመድ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ወደ ውስጥ ታግሎ ይዞ በመግባት ወደ ውስጥ የላካትን ኳስ ዩጋንዳዊው አጥቂ አህብዋ ብራያን በቀላሉ በማስቆጠር ወደ 2ለ1 ጨዋታው አሸጋግሮታል።

ቀዝቀዝ ያሉ እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በቀጠለው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበት እንጂ ንግድ ባንኮች በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ ሙከራን በማድረጉ ሻል ያለ መልክ ነበራቸው ለዚህም ማሳያው ፉአድ ፈረጃ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ እድሪስ አጎዶጆ የመለሳት ሙከራ ጠንከር ያለችዋ አጋጣሚያቸው ሆናለች።

ከዕረፍት በኋላ ዳግም በተመለሰው ጨዋታ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ከፍ ባለ ተነሳሽነት የተመለሱት ንግድ ባንኮች 46ኛው ደቂቃ በረጅሙ ከተከላካይ ክፍል ባሲሩ የደረሰውን ኳስ ለኪቲካ አቀብሎት አጥቂው ከግቡ ፊት ለፊት ተገናኘቶ የመታት ኳስ የግቡን ቋሚ ብረት ገጭታ ስትመለስ አዲስ ግደይ ሁለተኛዋን ዕድል አግኝቶ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

አጋማሹ ከተጀመረ ሦስት ደቂቃዎች ብቻ እንደተቆጠሩበት ከእጅ ውርወራ ኤፍሬም ያደረሰውን ኳስ አዲስ እና ኪቲካ ተቀባብለው ኪቲካ በመጨረሻም በጥሩ ዕይታ በተከላካዮች መሐል አሾልኮ ሲሰጠው ፉዓድ ፈረጃ ሦስተኛ ግብ አድርጓታል።

ድሬዳዋ ላይ እንደነበረው ቀዝቀዝ ያለ አየር ሁሉ ወጥ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች የተበራከቱበት ጨዋታው በአንፃራዊነት ንግድ ባንኮች አሁንም ኳስን ሲያገኙ ፈጠን ባለው የመስመር አጨዋወታቸው ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ ከራስ ሜዳ ከሚደረጉ ቅብብሎች ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል በመድረስ አልያም ደግሞ ረጃጅም በሆኑ ኳሶች ማጥቃት መርጠው ሲጫወቱ የታዩት አርባምንጮች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ ዕድሎችን ከመፍጠር አኳያ ደካሞች ነበሩ ፤ በዚህም ጨዋታው በንግድ ባንክ 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።