የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-1 አርባምንጭ ከተማ

“የሊግ ካምፓኒው ሕግ ያስከብራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።” አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ

“የመጀመሪያው 10 ደቂቃ የተጫዋቾቻችን የዕብደት ጊዜ ነበር ማለት እችላለሁ።” አሰልጣኝ በረከት ደሙ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታው አርባምንጭ ከተማን 3ለ1 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ በረከት ደሙ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ይታወቃል። ንግድ ባንክ ያለፈው ዓመት ቻምፒየን ነው። አብዛኛውን ስብስብ ይዞ ነው የቀጠለው ፤ በደንብ የተግባቡ እና ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች ይዟል። እኛም በተመሳሳይ በጥሩ አቀራረብ ለመቅረብ ነበር ያሰብነው። በእግርኳስ በጣም ወሳኝ የሚባሉ ደቂቃዎችን በአግባቡ ጨዋታውን መቆጣጠር ባለመቻላችን ዋጋ ከፍለናል። የመጀመሪያው 10 ደቂቃ የተጫዋቾቻችን የዕብደት ጊዜ ነበር ማለት እችላለሁ። ያ ዕብደት ዋጋ አስከፍሎናል። ያን ወደኋላ አስተካክለን ወደ ጨዋታው ለመግባት ጥረት አድርገን ነበር ፤ በዛም ጎል አግብተን የጨዋታውን ልዩነት ለማጥበብ ጥረት አድርገን ነበር። ከዕረፍት በኋላም ግን በተመሳሳይ ተከላካይ ክፍላችን ላይ የተፈጠረው ክፍተት በቀላሉ ጎል እንዲቆጠርብን አድርጎ ጨዋታው ከእጃችን እንዲወጣ አድርጎብናል።”

ከውጤት ማጣታችሁ አንጻር በዕረፍቱ ጊዜ ወደ ዝውውር የመግባት ሀሳብ አላችሁ?

“አዎ! አጋጣሚ ሆኖ ሦስቱንም ጨዋታ ተጋጣሚዎቻችንን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ዐይተን መግባን አልቻልንም። ይሄ ዲስአድቫንቴጅ ነው። በዛ ላይ ደግሞ ሦስቱም ተጋጣሚዎቻችን ሊጉ ላይ ጠንካራ ልምድ ያላቸው ጠንካራ ስብስብ የያዙ ናቸው። በዛ የተነሳ አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም። ባለው የዕረፍት ጊዜ ክፍተቶቻችን ላይ እና የተጫዋቾች መግባባት ላይ በደንብ ሠርተን ከዕረፍት መልስ ጠንካራ ቡድን ይዘን እንቀርባለን። ለእኛ የሚሆን ተጫዋች ካገኘን ወደ ዝውውር የምንገባባቸው ዕድሎች ይኖሩናል።”

አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው…

“ቆንጆ ጨዋታ ነበር። ከመጀመሪያው ጀምሮ ነው ጨዋታውን የተቆጣጠርነው። በመሃል እነሱን እንዲነሱ ያደረጋቸው አንዱ በእኛ የአቋቋም ስህተት አንድ ጎል አስቆጠሩ በኋላ ላይ ግን በድጋሚ ጨዋታውን ተቆጣጥረን እየመራን ወደ ዕረፍት ወጥተናል። በሁለተኛው አጋማሽም ያንኑ የማስቀጠል ሂደት ነው ያደረግነው። አጀማመራችንም ጥሩ ነበር በማስቆጠርም ሆነ ጨዋታውን በመቆጣጠር። በርካታ የግብ ዕድል መፍጠራችን የተሻለ ነበር። እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ቆንጆ ነው ማሻሻል ያለብንን ደግሞ እየሠራን እናሻሽላለን።”

ጨዋታውን እንዳልከው ተቆጣጥራችሁታል ፤ የዓምናው ቡድን ቀጥሏል ማለት ይቻላል?

“አይ እንደዛ ለማለት ጊዜው ገና ነው። ምናልባት የስኳድ ዴፕዝ ላይ ዐይተሃል ቤንች ላይ ያሉ ልጆችን ስታይ እንደዚህ ነው ማለት አይቻልም ግን እንደ መጀመሪያ መጥፎ አልነበረም እንደ መጀመሪያ ጨዋታ።”

ባልተለመደ ሁኔታ የፊት አጥቂ ተደርጎ ሁለት ጎሎችን ስላስቆጠረው ኪቲካ ጅማ…

“ኪቲካ ከዚህ በፊት አብሮኝ ስለሠራ ምን ጋ መጫወት እንደሚችል አውቀዋለሁ። በሁለቱም መስመሮችም ሆነ የፊት አጥቂ ሆኖ መጫወት ይችላል። ያንን ባሕሪውን ስለማውቅ ነው 9 ቁጥር ላይ ያጫወትኩት። ዛሬ የነበረው እንቅስቃሴው ደግሞ ቆንጆ ነው ሁለት ጎልም አስቆጥሯል። እንግዲህ ቀጣዩን ደግሞ አብረን የምናየው ይሆናል።”

የስኳድ ጥበት እንዳለ ነግረኸኛል ፤ ቡድኑን ለማጠናከር ተጨማሪ ተጫዋቾች ይመጡ ይሆን?

“የስኳድ ጥበቱን ያመጣው የደመወዝ ጣሪያው ነው። ተጫዋች ይመጣል ብለን የምንጠብቀው የለም። ከተፈቀደው ብር የሚተርፍ የለም። እኛ ሕጉን እና ሕጉን አክብረን ነው እየሠራን ያለነው። የሊግ ካምፓኒው ሕግ ያስከብራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ማለት ግልጽ የሆኑ ነገሮች ስላሉ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሁሉም እኩል መሥራት አለበት ብዬ አስባለሁ። ለዚህም ደሞ ያንን ዲቴል መርምረው እኩል ሕጉን ይተገብሩታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።”