የያሬድ ባየህ የመጨረሻ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ሲዳማ ቡናዎችን ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች።
ሲዳማ ቡናዎች መቻልን ካሸነፈው ቡድን መስፍን ሙዜ ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን፣ ኢማኑኤል ላርያ እና መስፍን ታፈሰ በመክብብ ደገፉ፣ ብርሀኑ በቀለ፣ አበባየሁ ሀጂሶ፣ በዛብህ መለዬ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ተክተው ሲገቡ ወልዋሎዎች በበኩላቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ ላይ እያሱ ለገሰ፣ ሚራጅ ሰፋ፣ ናሆም ኃይለማርያም፣ ገመቹ እና ሰመረ ኪዳነማርያም በታዬ ጋሻው፣ አላዛር ሽመልስ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና ዛሬ ጥዋት ዝውውራቸውን ያገባደዱት ዮናስ ገረመው እና ሳምሶን ጥላሁን ተክተው ገብተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ከመጨረሻው መርሃግብር በርከት ያሉ ቅያሬዎች አድርገው በጀመሩት ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር ቢያስመለክትንም የኋላ ኋላ የሲዳማ ቡናዎች ብልጫ የታየበት ነበር።
በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሙከራ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በሰባተኛው ደቂቃ ላይ መሪ ለመሆን ተቃርበውም ነበር ፤ ሀብታሙ ታደሰ ሳጥን ውስጥ ከመስመር ተሻምታ የወልዋሎ ተከላካዮች የመለሷት ኳስ አግኝቶ በመምታት በረከት አማረ በአስደናቂ ብቃት ያወጣት ኳስ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም በተጋጣሚ ተጫዋቾች ጫና ለቅብብል ስህተቶች ሲዳረጉ የተስተዋሉት ሲዳማዎች ከተጠቀሰው ሙከራ ውጭም በበዛብህ መለዬ ከቆመ ኳስ ያደረጋት ሙከራ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር ፤
አልፎ አልፎ በውስን ደቂቃዎች ኳስን ለመቆጣጥር ካሳዩት ሙከራ ውጭ በአብዛኛው ከኳስ ውጭ ጫና ፈጥረው በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሞከሩት ቢጫዎቹም በአንድ አጋጣሚ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርገዋል። ዳዋ ሆቴሳ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ያገኛት ኳስ በጥሩ ሁኔታ ለጋዲሳ መብራቴ አቀብሎት የመስመር ተጫዋቹ አክርሮ መቷት መክብብ ደገፉ ያዳናት ኳስም የቡድኑ የተሻለች ለግብ የቀረበች ሙከራ ነች።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ሲዳማ ቡናዎች ብልጫ በወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ግን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሙከራ ደራጃ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል።
ማይክል ኪፕሩቪ የወልዋሎ ተከላካዮች የቦታና ጊዜ አጠባበቅ ክፍተት ተጠቅሞ ከአማካይ ክፍል የተሻገረችለትን ኳስ በመምታት በረከት አማረ ባዳናት ሙከራ ጥቃታቸውን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በድጋሚ በአጥቂው አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ተጫዋቹ በሳጥኑ ቀኝ ጠርዝ አከባቢ ያገኛት ኳስ መቶ በረከት አማረ በድንቅ ብቃት ያዳናት ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።
በሰማንያ አራተኛው ደቂቃ ላይም ሀብታሙ ታደሰ ከተከላካይ መስመር በረዥሙ የተሻማችውን ኳስ ለመያዝ በሚያደርገው ጥረት ሳጥን ላይ ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት ሲዳማ ቡናዎች በተከላካዩ ያሬድ ባየህ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ችለዋል።
ሲዳማዎች ከግቡ በኋላም በፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተቃርበው የነበሩ ቢሆንም በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያዳረገው የወልዋሎ ግብ ጠባዊ በረከት አማረ እንደምንም አድኗታል።
ጨዋታው በሲዳማ ቡናዎች አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ተከታታይ ድል አስመዝግቦ ነጥቡን ስድስት ማድረስ ሲችል ወልዋሎዎችም ሦስተኛ ተከታታይ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።